በአዲስ አበባ በሺዎች የሚቆጠሩ ቤቶች ፈርሰዋል

ህዳር ፲፰ (አስራ ስምንት) ቀን ፳፻፭  ዓ/ም

ኢሳት ዜና:-የአዲስ አበባ መስተዳድር በአዲስ አበባ ከተማ በሁለት ክፍለ ከተሞች ብቻ ያፈረሳቸው ቤቶች በሺዎች የሚቆጠሩ መሆናቸውን አዲስ አበባ ከተማ የሚታተመው አዲስ ፎርቹን ጋዜጣ ዘገበ ።

ሳምንታዊው የእንግሊዘኛ ጋዜጣ አዲስ ፎርቹን እሁድ ዕለት እንደዘገበው በቦሌ ክፍለከተማና በንፋስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተሞች የፈረሱ ቤቶች 7ሺህ ደርሰዋል። መስተዳድሩ ከገበሬዎች በግዢ ወደ ነዋሪዎች የተላለፉት መሬቶች ሕጋዊ ማረጋገጫ የላቸውም በመለት እንዳፈረሳቸውም ተመልክቶዋል።

በንፋስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ በሐና ማርያም አካባቢ እንዲሁም በቦሌ ክፍለ ከተማ በቡልቡላ አካባቢ ህገ-ወጥ በሚል በአጭር ቀናት መስጠንቀቂያ የፈረሱት ቤቶች 7ሺህ መድረሳቸውን የገለጸው አዲስ ፎርቹን ጋዜጣ መስተዳድሩ ባስጠናው ጥናት በአዲስ አበባ ያለውን የቤት እጥረት ለመፍታት ተጨማሪ 360 ሺህ ቤቶች መገንባት እንደሚኖርባቸው አመልክቶዋል።

ከምርጫ 1997 ወዲህ በከተማዋ ሕገ-ወጥ ቤቶች መስፋፋታቸውን ከህዳር 2003 ጀምሮም ይኸው ሁኔታ መቀጠሉን ከዘገባው መረዳት ተችሎአል።

የአቶ መለስ መታመም መሰማቱና ሞታቸው መከተሉ ተጨማሪ ቤቶች እንዲገነቡ ምክንያት እንደሆነም አዲስ ፎርቹን ካጠናቀረው ዘገባ መረዳት ተችሎዋል።

ሰለባዎቹን በማነጋገር በአዲስ አበባ ከተማ በተለይ በሐና ማርያም አካባቢ ከ30 ሺህ ሰዎች በላይ መፈናቀላቸውን መዘገባችን ይታወሳል።