በአቶ በረከትና በአቶ ታደሰ ካሳ ላይ የ14 ቀን የጊዜ ቀጠሮ ተፈቀደ

(ኢሳት ዲሲ–የካቲት 19/2011)የአማራ ክልል ፀረ ሙስና ኮሚሽን መርማሪ በአቶ በረከት ስምዖንና አቶ ታደሰ ካሳ ላይ የጠየቀውን ተጨማሪ የ14 ቀን የጊዜ ቀጠሮ የባህር ዳርና አካባቢው ከፍተኛ ፍርድ ቤት ፈቀደ።

መርማሪው ትናንት ለችሎቱ ባቀረበው ማብራሪያ ባለፉት 14 ቀናት ያከናወናቸውን የምርመራ ስራዎች አስረድቷል።

በዚህም ከዘጠኝ ምስክሮች ቃል መውሰዱን እና በ20 ሰነዶች ላይ ምርመራ መድረጉን መርማሪው ገልጿል።

ባለፈው አርብም የዳሸን ቢራ አክሲዮን ማህበር ዳየት በሳሪ ለተባለው የእንግሊዝ ኩባንያ 90 ሚሊየን ዶላር የተሸጠ ቢሆንም አቶ በረከት ስምዖንና አቶ ታደሰ ካሳ የአክሲዮን ሽያጩን ለዳሽን ቢራ ወይም ጥረት ኮርፖሬት ገቢ አለማድረጋቸውን መርማሪው ገልጿል።

የፋብሪካው 50 በመቶ አክሲዮን ድርሻ በስዊዘርላንድ ባርክሌይስ ባንክ በግለሰብ በተከፈተ የሂሳብ ደብተር እንደሚገኝ በመጠርጠሩና ከዚህ ጉዳይ ጋር በተያያዘ በምስክርነት የሚፈለጉ ሁለት ሰዎች በውጭ ሀገር  የሚገኙ በመሆናቸው  መርማሪው ተጨማሪ የጊዜ ቀጠሮ ጠይቋል።

ግለሰቦቹ ከተጠረጠሩበት የሙስና ወንጀል ጋር በተያያዘ በውጭ ሀገራት ያሉ እነዚህን ሁለት የቃል ምስክሮችን አግኝቶ ቃል ለመቀበል እና የዳሸን ቢራ ፋብሪካ ኦዲት ያልተጠናቀቀ በመሆኑ እንዲሁም የአክሲዮን ሽያጩ ዓለም አቀፍ ህግ የተከተለ ስለመሆኑ ለመመርመር ተጨማሪ የ14 ቀናት የምርመራ ጊዜ እንዲፈቀድለት ነው የጠየቀው።

ተጠርጣሪዎቹ በበኩላቸው ከላይ የተጠቀሱት የኦዲት ስራዎች በተቋሙ አሰራር በየጊዜው ኦዲት ሲደረጉ መቆየታቸውን በመግለፅ የዳሸን ቢራ የአክሲዮን ሽያጭም ቢሆን በሀገሪቱ ህግ መሰረት ውልና ማስረጃ ያለው መሆኑን በማስረዳት መርማሪው የጠየቀውን ተማሪ የምርመራ ጊዜ ተቃውመዋል።

በሌላ በኩልም ተጠርጣሪዎቹ በማረሚያ ቤት ሆነው ጉዳዮችን እንዲያስፈፅሙ ኮምፒውተርና የስልክ አገልግሎት እንዲፈቀድላቸው ፍርድ ቤቱን ጠይቀዋል፤

የግራ ቀኙን የተመለከተው ፍርድ ቤቱ መርማሪ ፖሊስ የጠየቀው የ14 ቀናት ተጨማሪ የምርመራ ጊዜን ፈቅዷል።

የኮምፒውተር እና ስልክ አገልግሎትን በተመለከተ ግን በማረሚያ ቤት ሁለቱ ግለሰቦች እንደማንኛውም ታራሚ እንደሚታዩ በመግለፅ፥ በተለየ ለእነሱ የሚቀርብ የኮምፒውተርና የስልክ አገልግሎት አይኖርም ሲል ጥያቄያቸውን ውድቅ አድርጓል።