በአርባ ምንጭ በተነሳው ውዝግብ የታሰሩ 28 ሰዎች አለመለቀቃቸው ታወቀ

ኢሳት ዜና:-ግለሰቦቹ የታሰሩት አካባቢውን ህዝብ ለአድማ ለማነሳሳት ሙከራ አድርጋችሁዋል ተብለው ነው።

ግለሰቦቹ ከዚህ ቀደም የመንግስት ባለስልጣናት የአካባቢውን ደን በመመንጠር ሰፋፊ ቤቶችን ለግል የመኖሪያ ቤቶች ግንባታ አውለዋል በሚል መታሰራቸው ይታወቃል።

እስረኞቹ አቤቱታቸውን እስከ ጠቅላይ ሚኒሰትሩ ድረስ ቢያቀርቡም ሰሚ አጥተው ከቆዩ በሁዋላ፣ የአካባቢው ባለስልጣናት ለምን አጋላጣችሁን በሚል ሰብስበው ማሰራቸው ታውቋል።

ምንም እንኳ ግለሰቦቹ ያቀረቡት አቤቱታ መንግስት ዘግይቶም ቢሆን ትክክል ነው ቢልም ፣ አቤቱታ አቅርቢዎቹ ግን እስካሁን አለመፈታታቸውን የአካባቢው ሰዎች ተናግረዋል።

መንግስት በአካባቢው ያለውን ውጥረት ለማብረድ አንዳንድ ባለስልጣናቾችን ከስራ እና ከደሞዝ ማገዱን ተከትሎ በአካባቢው አሁንም የጸጥታ ስጋት መኖሩን የአካባቢው ነዋሪዎች ገልጠዋል።

በሌላ ዜና ደግሞ በከተማዋ ከትናንት ጀምሮ ትራንስፖርት ተቋርጦ እንደነበር ዘጋቢያችን ገልጧል። የትራንስፖርት አድማ የተደረገው አዲሱን ታሪፍ ተከትሎ ነው።

የህዝብ ማመላለሻ መኪኖች ባለንብረቶች ባደረጉት አድማ ህዝቡ በአይሲዙ መኪና ሲመላለስ ውሎአል። በከተማዋ ትምህርት ቤቶች ተዘግተው የኢህአዴግ ካድሬዎች ለተማሪዎች ስለጸጥታ፣ ሀይማኖትና መሰል ጉዳዮች ትምህርት እየሰጡ መሆኑ ታውቋል።