በአምቦ ዩኒቨርስቲ ተማሪዎች ተጎዱ

(ኢሳት ዲሲ–ጥር 3/2010)

በአምቦ ዩኒቨርስቲ በተነሳ ተቃውሞ ተማሪዎች መጎዳታቸው ታወቀ።

ባለፈው እሁድ የገና በአል ላይ በምግብ አዳራሽ ውስጥ የተቀሰቀሰውን ተቃውሞ ተከትሎ ግጭት መፈጠሩ የታወቀ ሲሆን እስከትላንት ድረስም መቀጠሉ ታውቋል።

በዩኒቨርስቲው የሰፈረው የአጋዚ ሰራዊት ተማሪዎች ላይ ክፈኛ ድብደባ መፈጸሙን ተከትሎ የዩኒቨርስቲው ፕሬዝዳንት ለትምህርት ሚኒስቴር የቅሬታ ደብዳቤ መላካቸውን የደረሰን መረጃ ያመለክታል።

የተወሰኑ ተማሪዎች ግቢውን ለቀው ወተዋል።

የዩኒቨርስቲው ፕሬዝዳንት ትምህርት ሚኒስቴር ጥቃት የፈጸሙትን የጸጥታ ሃይሎች ጉዳይ እንዲያጣራ ጠይቀዋል።

በሌላ በኩል በአዳማ ዩኒቨርስቲ ተማሪዎች በታጣቂዎች ታጅበው ወደ መማሪያ ክፍላቸው እንደሚሄዱ ታውቋል።             

ተቃውሞ ተለይቶት የማያውቀው የአምቦ ዩኒቨርስቲ ሰሞኑን ቀውስ ገጥሞት ሰንብቷል።

ያለፈው እሁድ የገና በዓል የአውዳመት ዝግጅት ላይ በተፈጠረው ተቃውሞ በግቢው ሰፍሮ የሚገኘው የአጋዚ ጦር በተማሪዎች መኝታ ክፍል ሰብሮ በመግባት ድብደባ መፈጸሙን የደረሰን መረጃ ያመለክታል።

ካለፈው እሁድ ጀምሮ በዩኒቨርስቲው ተቃውሞ እየተደረገ መሆኑን የሚገልጹት የኢሳት ምንጮች የተጎዱ ተማሪዎች ቁጥር ለመግለጽ እንደማይቻል ጠቅሰዋል።

ሰኞ ምሽት ከፍተኛ የተኩስ ድምጽ ይሰማ እንደነበርም ተናግረዋል። በአሁኑ ሰዓት ተማሪዎች ከመኝታ ክፍላቸው መውጣት አልቻሉም። ምግብ መኝታ ክፍላቸው ድረስ ይላክላቸዋል ሲል አንድ በአካባቢው የነበረ ወጣት ለኢሳት ገልጿል።

የባለፈው እሁድን ግጭት ተከትሎ የተከሰተውን ጉዳት በመጥቀስ የአምቦ ዩኒቨርስቲ ፕሬዝዳንት ለትምህርት ሚኒስቴር የቅሬታ ደብዳቤ መላካቸው ታውቋል።

በአቶ ታደሰ ቀነአ አመንቴ የአምቦ ፕሬዝዳንት ስም በወጣው ደብዳቤ ላይ እንደተገለጸው የመንግስት የጸጥታ ሃይሎች ሰኞ ምሽት 87 የመኝታ ክፍሎች በርን ሰብረው በመግባት ተማሪዎች ላይ ከፍተኛ ድብደባ ፈጽመዋል።

በዚህም በርካታ ተማሪዎች የአካልና የስነልቦና ጉዳት ደርሶባቸዋል።

ያለበቂ ምክንያት ታጣቂዎች በር ሰብረው ተማሪዎችን መደብደባቸውን ያወገዙት የዩኒቨርስቲው ፕሬዝዳንት ትምህርት ሚኒስቴር በአስቸኳይ ጉዳዩን እንዲያጠራውና ተጠያቂ በሆኑ ግለሰቦች ላይ ተገቢው ርምጃ እንዲወሰድ የዩኒቨርስቲው ፕሬዝዳንት ጠይቀዋል።

በትምህርት ሚኒስቴር በኩል የተሰጠ ምላሽ ስለመኖሩ የታወቀ ነገር የለም።

በሌላ በኩል በአዳማ ዩኒቨርስቲ አለመረጋጋቱ እንደቀጠለ ነው ሲሉ የኢሳት ምንጮች ገልጸዋል።

ባለፈው ሳምንት 18 ተማሪዎች ከተባረሩ በኋላ ውጥረቱ የጨመረ መሆኑ ታውቋል።

በየዕለቱ በማንኛውም ሰዓት የአጋዚ ወታደሮች ድንገት ወደተማሪዎች መኝታ ክፍሎች በመግባት ፍተሻ ያደርጋሉ ተብሏል።

ተማሪዎች ወደመማሪያ ክፍላቸው ሲሄዱና ሲመለሱ በአጋዚ ወታደሮች ታጅበው መሆኑም ተመልክቷል።

በኢትዮጵያ ከሚገኙ 36 ዩኒቨርስቲዎች በ20ዎቹ የመማር ማስተማር ሂደቱ መስተጓጎሉ ይነገራል።

በአብዛኞቹ መረጋጋት እንደሌለ መረጃዎች ያመለክታሉ።

ብሄራዊ የደህንነት ምክር ቤት ሰሞኑን በሰጠው መግለጫ በስም ባልጠቀሳቸው ሶስት ዩኒቨርስቲዎች ትምህርት መቋረጡን አስታውቋል።

ከ1ሺህ በላይ ተማሪዎች መባረራቸውንም ጠቅሷል።