በአሜሪካ ሲያትል ከተማ አንድ ኢትዮጵያዊ ባህር ውስጥ ሰጥሞ ሕይወቱ አለፈ

(ኢሳት ዜና–ሐምሌ 18/2009) ይትባረክ ደሞዝ የተባለው የ36 አመት ኢትዮጵያዊ ወጣት ህይወቱ ያለፈው ባለፈው እሁድ ሲሆን አስከሬኑ የተገኘው ከ24 ሰአት ፍለጋ በኋላ ነበር።

በአሜሪካ ዋሺንግተን ግዛት ሲያትል ከተማ ነዋሪ የሆነው ይትባረክ ደሞዝ እሁድ ማለዳ ሊነጋጋ ሲል ከሚነዳት ጀልባ ዘሎ ባህር ውስጥ ከገባ በኋላ ህይወቱ ማለፉ ተመልክቷል።

በአካባቢው የነበሩ የአይን እማኞች እንደገለጹት ወጣቱ ከመዝለሉ በፊት ከጀልባዋ ውስጥ የሚረብሽ ከፍተኛ ድምጽ ተሰምቷል።

ይህንን ተከትሎ ከጀልባዋ ዘሎ ከወጣ በኋላ የደረሰበት ባለመታወቁ 24 ሰአታት ከፈጀው ፍለጋ በኋላ አስከሬኑ መገኘቱ ተመልክቷል።

የዋና ችሎታ እያለው በህር ውስጥ መስጠሙ በቅርብ ለሚያውቁት ያልተጠበቀ ክስተት እንደሆነባቸ ነው የተናገሩት።

በጥረቱ ውጤታማ ነው የሚባለውና የራሱን አነስተኛ የትራንስፖርት ድርጅት በማቋቋም ህይወቱን የሚመራው ይትባረክ ደሞዝ የ2 ልጆች አባት ነበር።

በሲያትል ከተማ ነዋሪ የሆነው የሟች ጓደኛ ዶክተር ሼክስፔር ፈይሳ ኮሞ ኒውስ ለተባለው የከተማዋ መገናኛ ብዙሃን በሰጠው አስተያየት የይትባረክ ህልፈት በአካባቢው ለሚኖሩ ኢትዮጵያዊ ማህበረሰብ አስደንጋጭ ዜና መሆኑን ገልጸዋል።

በማህበረሰቡ ውስጥ ችግር በገጠመ ቁጥር ግንባር ቀደምና ለተቸገሩ ደራሽ ነበር ብሏል።

በሲያትል ሌክ ዩኒየን በተባለው ሃይቅ ላይ በደረሰበት አደጋ ህይወቱ ያለፈውን ይትባረክ ደሞዝን ለማሰብ በሲያትል መካነ ብርሃን ቅዱስ ገብርኤል ቤትክርስቲያን ዝግጅት መደረጉን ለማወቅ ተችሏል።

ይትባረክ ደሞዝ አሜሪካ ከገባ 15 አመታትን ማስቆጠሩ ተመልክቷል።