በአሜሪካ-ሚኒሶታ ለመጀመሪያ ጊዜ የኢትዮጵያ ቀን ፌስቲቫል ሊካሄድ ነው::

በአሜሪካ-ሚኒሶታ ለመጀመሪያ ጊዜ የኢትዮጵያ ቀን ፌስቲቫል ሊካሄድ ነው::
( ኢሳት ዜና ነሐሴ 09 ቀን 2010 ዓ/ም ) የ10 ሺህ ሃይቆች ባለቤት ተብላ በምትታወቀው የአሜሪካዋ ግዛት ሚኒሶታ በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ የኢትዮጵያ ቀን ፌስቲቫል ሊከበር ዝግጅቱ እየተጠናቀቀ መኾኑን የፌስቲቫሉ አስተባባሪዎች በተለይ ለኢሳት ገልጸዋል። ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ወደ ሚኒሶታ በተጓዙበት ወቅት በተሰናዳው ዝግጅት ላይ በኢትዮጵያውያኑ መከከል መለስተኛ ውጥረት ተከስቶ እንደነበር ይታወሳል።
ከዚያም ባሻገር የልዩ ልዩ ብሔረሰብ ባህላዊ ዳንሶችን ያሳዩት ልጆች የአማርኛ ውዝዋዜ ባለማሳዬታቸው ጠቅላይ ሚኒስትሩ በልጆቹ ስም ይቅርታ እስከመጠየቅ መድረሳቸው አይዘነጋም። የዚያ ዓይነት አለመግባባት የተከስተው ማህበረሰባችን ባለመጠናከሩ ምክንያት ነው ያሉ በሺህዎች የሚቆጠሩ በሚኒሶታ ነዋሪ ኢትዮጵያውያን ከሰሞኑ ኮሚኒቲያቸውን በከፍተኛ ጥንካሬ ሲያዋቅሩ ከሰነበቱ በኋላ ነው በከተማቸው የመጀመሪያውን ፌስቲቫል ለማድረግ የወሰኑት። በፈረንጆቹ አቆጣጠር የፊታችን ሴፕቴምበር ሁለት ቀን ፣ በግዙፍ ስታዲየም ውስጥ በሚካሄደው በዚሁ የኢትዮጵያውያን ቀን ፌስቲቫል- የሙዚቃ ትዕይንት፣ የፋሽን ሾው፣ ባህላዊ ዝግጅት፣እንዲሁም በሚኒሶታ የኢትዮጵያና በኤርትራ ቡድኖች መካከል የሚደረግ የፍቅር እግር ኳስ ጨዋታ ይደረጋል።
የስዕል ኤግዚብሽን እና የኢትዮጵያን ባህላዊ አልባሳትና ምግቦች የሚያስተዋውቁ ዝግጅቶም በዝግጅቱ ውስጥ መካተታቸውን አስተባባሪዎቹ አመልክተዋል።
በዚህ የመጀመሪያ በሆነው ታላቅ የኢትዮጵያ ቀን ፌስቲቫል ላይ ታዋቂው ድምጻዊ ስለሺ ደምሴ በቅጽል ስሙ ጋሽ አበራ ሞላ አርቲስ ብርሃኑ ተዘራ፣ አርቲስት ሙክታር አዴሮ ፣አርቲስት ያህያ አደም፣አርቲስት ገነት አባተ፣አርቲስት በረከት ዓለም እና የኢትዮጵያን ብሄር ብሄረሰብ ዘፈኖችን የሚያቀርቡ ሌሎችም ድምጻውያን ተጋብዘዋል። ሜሪ ጆይ ኢትዮጵያን ጨምሮ መቀመጫቸውን ሃገር ቤት ያደረጉ የግብረ ሠናይ ድርጅቶችም የዚሁ ፌስቲቫል አካል እንደሚሆኑ ታውቋል። በፌስቲቫሉ ላይ በሚኒሶታ እና በተለያዩ የአሜሪካ ግዛቶች የሚኖሩ በብዙ ሺህዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን ይገኛሉ ተብሎ ይጠበቃል።