በአልቃይዳ ምክንያት የኢትዮጵያ አየር መንገድ ሸኚዎች እንዳይገቡ አገደ

ሚያዚያ ፲፫ (አስራ ሦስት) ቀን ፳፻፬ ዓ/ም

ኢሳት ዜና:-አየር መንገዱ ሸኚዎች ወደ ውስጥ እንዳይገቡ ያገደው ከአራት ቀናት በፊት ጀምሮ ነው። የፋሲካ በአልን ለማክበር ወደ ኢትዮጵያ የተጓዙ መንገደኞች ወደ አየር ማረፊያው ሲገቡ ከወትሮው የተለየ ጥብቅ ፍተሻም እየተካሄደባቸው ነው። ተጓዦችን ለመሸኘት የመጡት ግን ወደ ውስጥ እንዳይገቡ ተደርጓል። ወደ ውስጥ ሲገቡና ሲወጡ የሚታዩት ልዩ የይለፍ ወረቀት የያዙ የመንግስት ባለስልጣናት ብቻ ናቸው። በርካታ ሸኚዎች በድርጊቱ ማዘናቸውን አካባቢውን ለጎበኘው የኢሳት ሪፖርተር ገልጠዋል።

አንድ ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣን አየር መንገዱ እገዳውን ላልተወሰነ ጊዜ የጣለው አልቃይዳ የሽብር ጥቃት ለመፈጸም መዘጋጀቱን መንግስት መረጃ ስለደረሰው ነው ብለዋል። ሰሞኑን አቶ መለስ በኢትዮጵያ አንዳንድ አካባቢዎች የአልቃይዳ ሴል ተገኝቷል ብለው መናገራቸው ይታወሳል፤ ከወር በፊት ደግሞ  የአልቃይዳ አባላት ናቸው የተባሉ 3 ኢትዮጵያውያን  ታስረው ፍርድ ቤት ቀርበዋል።

አንዳንድ ወገኖች የአልቃይዳ መረብ አለ የሚለውን በጥርጣሬ አይን እየተመለከቱት ነው። መንግስት ከሙስሊም ኢትዮጵያውያን የተነሳበትን ከፍተኛ ተቃውሞ ለመጨፍለቅ አልቃይዳን በማስፈራሪያነት ሊጠቀምበት አስቦአል ይላሉ እነዚህ ወገኖች። ምናልባትም በኢትዮጵያ አየር መንገድ ውስጥ በአንድ የአረጀ አውሮፕላን ላይ መንግስት እራሱ ያቀነባራረው ጥቃት ሊፈጸም ይችላል የሚሉ ፍንጮችም አሉ።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ሸኚዎችን ለሳምንት ያክል ሲያግድ የአሁኑ የመጀመሪያው ነው ተብሎአል።

___________________________________________________________________________________________________________________________________________________

ESAT is the first independent Ethiopian satellite service tasked to produce accurate and balanced news and information, as well as other entertainment, sports and cultural programming created for and by Ethiopians.

ESAT is committed to the highest standards of broadcast journalism and programming and will strive to provide an outlet of expression to all segments of the diverse Ethiopian community worldwide