በብአዴን ድርጅታዊ አመራር አባላት መካከል የተከሰተው ውዝግብና አለመግባባት ተባብሶ መቀጠሉ ተሰማ

(ኢሳት ዜና–መስከረም 15/20015) በብአዴን ድርጅታዊ አመራር አባላት መካከል የተከሰተው ውዝግብና አለመግባባት ተባብሶ መቀጠሉን የኢሳት ምንጮች ገለጹ።

የድርጅቱ ማእከላዊ አባላት እና የክልሉ ምክር ቤት ሳይስማሙበት አቶ ገዱ አንዳርጋቸው የተፈራረሙት የግጨው ስምምነት ለውዝግቡ ዋነኛ መንስኤ እንደሆነ ተገልጿል።

የሞባይል ስልክ እንዳይገባ ተደርጎ በሚስጥርና በጭቅጭቅ የተካሄደው የብአዴን ከፍተኛ አመራር አባላት ስብሰባ የቃላት ልውውጥ ደርሶናል።

የትግራይ እና የአማራ ክልሎች ፕሬዝዳንቶች የተፈራርሙት የግጨው ስምምነት በተወሰኑ ሰዎች እውቅና በሕወሐት ተጽእኖ የተካሄደ ነው።
በብአዴን አመራር አባላት መካከል ከፍተኛ ውዝግብ የተነሳበትና ያለ ስምምነት ለመቋረጡ ምክንያት የሆነውም ይህ አጀንዳ ሆኗል ።

በዚህ ዙሪያ ላይ የድርጅቱ ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ አለምነው መኮነን ለረዥም ጊዜ በሁለቱ ክልሎች እና ድርጅቶች መካከል መከፋፈልና ለጎሪጥ መተያያ ሆኖ የቆየው የትግራይ እና የአማራ የወሰን የይገባኛል ውዝግብና የግጨው ጉዳይ እጅግ በሰከነ እና ህዝብን ባማከለ መንገድ መፍትሔ አግኝቷል ሲሉ ሪፖርታቸውን አቅርበዋል።

ይህን ጉዳይ ማዕከላዊ ኮሚቴው ተቀብሎ ለድርጅቱ አባላትና ለህዝቡ እዲያሳምን ስራ አስፈፃሚው ወስኗል በሚል ሪፖርታቸውን ያጠቃለሉት አቶ አለምነው ከመድረኩ ያገኙት ምላሽ ግን ጩሆትና ተገቢ ያልሆኑ ቃላቶችን ነበር።
የብአዴን ሊቀመንበር አቶ ደመቀ መኮንን በጩሕት የተሞላውን አዳራሽ ለማረጋጋት መሞከራቸው ተሰምቷል።

ነገር ግን የድርጅቱ የማዕከላዊ ኮሚቴ አባል ዶክተር አምባቸውን ጨምሮ ሌሎቹ የማዕከላዊ ኮሚቴ አባላትም የቀረበው ሪፖርት ግልጽነት የጎደለውና የትኛውንም የድርጅት አባልም ሆነ ህዝብን የማይወክል መሆኑን ቁጣ በተሞላበት ድምጽ ተናግረዋል።

መድረኩን የሚመሩት አቶ ደመቀ መኮንን በቁጣ አቅጣጫውን እየሳተ ያለውን መድረክ ለማስተካከል ቢሞክሩም አልተሳካላቸውም ይላሉ የኢሳት ምንጮች።

ስነ ስርአት የሚለውን ማስጠንቀቂያ ወደ ጎን በማለት ጥያቄያቸውን የቀጠሉት ዶክተር አምባቸው አቶ ገዱ ስምምነቱን የፈረመው በክልል ርዕሰ መስተዳድር ስልጣን ከሆነ የትኛውን የካቢኔ አባላትን ሰብስቦና አነጋግሮ ነው? በዚህ ጉዳይስ የክልሉ የምክር ቤት አባላት ሊነጋገሩበት አይገባም ነበር ወይ? ቀጣይ በምክር ቤት ስብሰባ ላይ ስምምነቱ ህገ ወጥ ነው አንቀበለውም ቢባልስ የሚል ጥያቄ አከታትለው ለመድረኩ አቅርበዋል።

አቶ አለምነው ሪፖርቱን ሲያቀርቡም ትልቅ ድል እደሆነ እና ስምምነቱም የሁለቱ ድርጅቶች ነው የተባለውም በጭራሽ አባላቱንም ሆነ ሕዝቡን የማይወክል ነው በማለት ተቃውሞአቸውን አሰምተዋል።

የትኛውም አባል ሆነ ሕዝብ ባልተወያየበትና ገዱ ብቻ በተፈራረመው ተቀበሉ እንዲሁም ለአመራሩ አሳምኑ መባሉ ፌዝ ነው በማለት ሃሳባቸውን ሲገልጹ የስብሰባው ተሳታፊዎች በጭብጨባ ድጋፋቸውን ገልጸዋል።
አቶ ደመቀ ስነ ስርአት በማለት ዶክተር አምባቸውን በማቋረጥ መድረኩን ዝም ለማሰኘት ያደረጉት ሙከራ እንዳልተሳካ ምንጮቹ ይናገራሉ።

ዶክተር አምባቸው አሁንም ቢሆን ውሳኔውን በግልም ቢሆን እንደማይቀበሉት ደጋግመው ለመድረኩ ተናግራዋል።

የሁለቱ ክልሎች ኮሚኒኬሽን ቢሮዎች የሰጡት መግለጫ በራሱ ሂደቱ ግልጽነት የጎደለው መሆኑን ያመላክታል በሚል በሰጡት አስተያየት ከተሰብሳቢው ድጋፍ በማግኘታቸው በድጋሚ እንዳይናገሩ በአቶ ደመቀ ተከልክለዋል።

በስብሰባው ላይ የተገኙት አቶ በረከት ስምኦንም በከፍተኛ ተቃውሞ የተናጠውን ስብሰባ ለማረጋጋት ሲፍጨረጨሩ ተስተውለዋል ሲሉ የኢሳት ምንጮች ገልጸዋል።