በቤንች ማጂ በተከሰተ ግጭት ከ150 በላይ ሰዎች ተገደሉ

ታህሳስ  ፳፮(ሃያ ስድስት) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም

ኢሳት ዜና:-በደቡብ ክልል በቤንቺ ማጂ ዞን በቤሮ ሻሻ ወረዳ በሳሊ ቀበሌ በሚገኝ ባህላዊ የወርቅ ማዕድን ማውጫ መንደር በተከሰተው የእርስ በርስ ግጭት  ከ 162 ሰዎች በላይ መገደላቸው ታውቋል::

የአካባቢው የኢሳት የመረጃ ምንጭ እንደገለጸው  መንግስት የፌደራል ፖሊስ ሀይሎችን በስፍራው  ቢያሰማራም የክልሉ መንግስት የራሳችንን የውስጥ ችግር ራሳችን ነን የምንፈታው የሚል አቋም በመያዙ የፌደራል ፖሊስ ሀይሎች ወደ አካባቢው እንዳይደረሱ ተደርጓል።

ይህን ዜና እስካጠናከርንበት ጊዜ ድረስ በእየቀኑ  እስከ 9 የሚደርሱ ሰዎች እየተገደሉ ነው::  ከ 20 ቀን በፊት ፖሊስ የአካባቢውን ህብረተሰብ አስቸኳይ ስብሰባ በመጥራት ማንነቱ ያልተለየ የ 6  ቀን አስክሬን ከጉድጏድ በማውጣት ከተሰበሰበው ህዝብ የተወሰኑትን በመመልመል በዱላ ደብድቧል:: ተደብዳቢዎቹ  በምንም ወንጀል የተጠረጠሩ እንዳልነበሩ ታውቋል::

የወረዳውን ባለስልጣናት ለማግኘት ያደረግነው ሙከራ አልተሳካም።