በቤንሻንጉል የአማራ ተወላጆች በመስጊድ ውስጥ ተጠልለዋል ተባለ

(ኢሳት ዲሲ–ታህሳስ 3/2011) ቤንሻንጉል ጉምዝ ካማሼ ዞን ያሶ ወረዳ የተፈናቀሉ ከ900 በላይ የአማራ ተወላጆች በምስራቅ ወለጋ መስጊድ ውስጥ ተጠልለው እንደሚገኙ ተገለጸ።

ወደ አማራ ክልል በመጓዝ ላይየሚገኙት እነዚህ ተፈናቃዮች መንግስት ይድረስልን ሲሉ ጥሪ አድርገዋል።

በምስራቅ ወለጋ አንገር ጉቴ ከተማ በሚገኝ መስጊድ ውስጥ የተሰባሰቡት ተፈናቃዮች ቁጥር በየዕለቱ በመጨመሩ ከፍተኛ ችግር እንደደረሰባቸው ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

ባለፈው ሳምንት ከካማሼ ዞን ያሶ ወረዳ የተፈናቀሉ 600 የሚሆኑ የአማራ ተወላጆች ባህርዳር የገቡ ሲሆን እስካሁን ምንም ዓይነት ድጋፍ እየተደረገላቸው አለመሆኑን ገልጸዋል።

ቤንሻንጉል ጉምዝ ክልል የጸጥታው ሁኔታ አሳሳቢ እየሆነ መጥቷል።

በተለይም ካማሼ ዞን ከመንግስት ይልቅ የተለያዩ ዓላማ ያላቸው ታጣቂ ቡድኖች ያሻቸውን የሚያደርጉበት፣ወታደራዊ ስልጠና የሚሰጡበት፣ የታጠቁ አባላቶቻቸውን ወደ ስምሪት የሚልኩበት፣ ከአጎራባች ዞኖችና የኦሮሚያ ክልል አካባቢዎች ዝርፊያ ለመፈጸም የሚነሱበት፣ ግድያን ጨምሮ የተለያዩ ጥቃቶችን በሰላማዊ ዜጎች ላይ ለመፈጸም በሙሉ ሃይላቸው የሚንቀሳቀሱበት ጠንካራ ይዞታቸው እንደሆነ ነው የሚነገረው።

ለ100ሺህ የኦሮሞና የአማራ ተወላጆች መፈናቀል፣ ከ100 በላይ ለሚሆኑ ዜጎች መገደል መነሻ የሆነው የ5 የቤንሻንጉል ጉምዝ ካማሼ ዞን አመራሮች ግድያ የተፈጸመውም በዚሁ ዞን ነው።

ሰሞኑን የብሔራዊ አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን እንዳስታወቀው የእርዳታ እህል ለማከፋፈል ወደ ካማሼ ዞን የሄዱ ከባድ ተሽከርካሪዎች በእነዚሁ ቡድኖች ጥቃት የተነሳ መመለስ አልቻሉም።

የእርዳታ እህል ለማከፋፈል የጸጥታው ሁኔታ እንዳላመቸ ኮሚሽኑ ገልጿል።

እናም ካማሼ ዞን ቀውስ የበረታባት፣ ጸጥታው የደፈረሰባት፣ የሰው ልጅ መከራ የበዛባት ከሆነች ወራት አለፏት።

የአማራ ብሔር ተወላጆች በቤንሻንጉል ጉምዝ ክልል የጥቃት ሰለባ ሲሆኑ የካማሼው የመጀመሪያው አይደለም።

ከአራት ዓመት በፊትም በ10ሺዎች የሚቆጠሩ የአማራ ተወላጆች ላይ የደረሰው መጠነ ሰፊ መፈናቀል ከፍተኛ ሰብዓዊ ጥፋት ማስከተሉ የሚታወስ ነው።

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ ለአማራና ኦሮሞ ተወላጆች የስቃይ ቀጠና በመሆን የምትጠቀስ ዞን ሆናለች ካማሼ።

ከአራት ወራት በፊት በቤንሻንጉል ጉምዝና ኦሮሚያ አዋሳኝ አካባቢዎች ለተፈጠረው ቀውስ ማዕከል በመሆን የምትነሳውም ካማሼ ዞን ናት።

ከዚሁ ዞን ደግሞ ያሶ በተባለ ወረዳ ያለው ችግር የጠና እንደሆነ ነው ካለፈው ሳምንት ጀምሮ ተፈናቅለው ምስራቅ ወለጋና ባህርዳር የደረሱ የአማራ ተወላጆች የሚገልጹት።

በማንነታቸው ምክንያት ለጥቃት የተዳረጉት የአማራ ተወላጆች ከያሶ ወረዳ የተለያዩ ቀበሌዎች ሀብት ንብረታቸውን ጥለው በመሰደድ ላይ ናቸው።

ባለፈው ሳምንት 600 የሚሆኑት ባህርዳር ደርሰዋል።

ከምስራቅ ወለጋ የደረሰን መረጃ እንደሚያመለክተው ደግሞ ከ900 በላይ የአማራ ተወላጆች በዞኑ አንገር ጉቴ ከተማ በሚገኝ ቶፊቅ በተሰኘ መስጊድ ተጠልለዋል።

ተፈናቃዮቹ እንደሚናገሩት በያሶ ወረዳ የሚንቀሳቀሱ ታጣቂ ሃይሎች በጥይትና በቀስት በርካታ ሰዎችን ገድለዋል።

ከማሳቸው ላይ ወድቀው የቀሩ ዘመድ ጓደኞቻቸውን በሀዘን እያስታወሱ የሚገልጹት ተፈናቃዮች ህይወታቸውን ለማትረፍ ለረጅም ቀናት በእግር በመጓዝ ከአንገር ጉቴ ከተማ መድረሳቸውን ተናግረዋል።

አንገር ጉቴ ሲደርሱ የከተማው አስተዳደር ድጋፍ ሊያደርግላቸው ባለመቻሉ በመስጊድ ለመጠለል መገደዳቸውን ይገልጻሉ።

ቁጥራቸው ከዕለት ወደ ዐለት እየጨመረ በመምጣቱም የሚበላና የሚጠጣ ማግኘት እንደተቸገሩ ነው ተፈናቃዮቹ የሚናገሩት።

መንግስት አፋጣኝ ምላሽ እንዲሰጣቸውም ጠይቀዋል።

በተመሳሳይ ባህር ዳር የደረሱት ተፈናቃዮችን ለመርዳት አልተዘጋጀሁም ባለው የአማራ ክልል መንግስት መማረራቸው ያገኘነው መረጃ ያመልክታል።

ኢትዮጵያውያን ለእነዚህ ወገኖች የሚችሉትን እንዲያደርጉም ጥሪ ቀርቧል።