በቢልና ሚሊንዳ ጌት ፋውንዴሽን እንዲሁም በሌሎች ለጋሾች የሚሰጠው ድጋፍ ለአማካሪ ድርጅት በሚደረግ ክፍያ እየባከነ መሆኑ ተገለጸ

(ኢሳት ዜና–መስከረም 11/2010) የኢትዮጵያን የግብርና ስርአት ለማሻሻልና አርሶአደሮችን ተጠቃሚ ለማድረግ በቢልና ሚሊንዳ ጌት ፋውንዴሽን እንዲሁም በሌሎች ለጋሾች የሚሰጠው ድጋፍ ከተግባራዊ ስራ ይልቅ ለአማካሪ ድርጅት በሚደረግ ክፍያ እየባከነ መሆኑን ምንጮች ገለጹ።

የኢትዮጵያ ግብርና ማበልጸጊያ ማእከል ዋና ዳይሬክተር አቶ ካሊድ ቦምባ የዘመዶቻቸው ንብረት ለሆነውና ፈርስት ኮልሰንታሲ ለተባለው ድርጅት በእርዳታ የሚመጣውን ገንዘብ እያሻገሩ እንደሆነም ተመልክቷል።

የጉዳዩን አሳሳቢነት በተመልከተ የሚመለከታቸው አካላት ለጸረ ሙስና ኮሚሽን እንዲሁም ለቢልና ሚሊንዳ ጌት ፋውንዴሽን አቤቱታ ማቅረባቸውንም ለኢሳት የደረሰው ዜና ያመለክታል።

የኢትዮጵያን ግብርና ለማዘመንና አርሶ አደሩን ተጠቃሚ ለማድረግ በቢልና ሚሊንዳ ጌት ፋውንዴሽን ድጋፍ የተቋቋመው የግብርና ማበልጸጊያ ተቋም ስራን በሃላፊነት እንዲመሩ አቶ ካሊድ ቦምባ የተባሉ አሜሪካዊ ዜግነት ያላቸው ኢትዮጵያዊ ተወላጅ ወደ ኢትዮጵያ መሄዳቸውንና ለሶስት አመት በኮንትራት እንዲሰሩ መወሰኑን ምንጮች ገልጸዋል።

ሆኖም ግለሰቡ የኮንትራት ጊዜያቸው ካለፈ ሶስት አመት ቢቆጠርም ምንም አይነት የተጨበጠ ነገር ባለመታየቱ ጥረቱ መክሸፉን ምንጮቹ ይገልጻሉ፡፡

ይህ ሁሉ ሆኖ ግን አቶ ካሊድ ቦምባ አሁንም በሃላፊነታቸው ላይ መሆናቸውን መረጃው ያመለክታል።

በእቅዱ መሰረት ከሶስት አመት በኋላ አቶ ካሊድ ቦምባ በኢትዮጵያዊ ዜጋ እንዲተኩ የተወሰነ ቢሆንም ተግባራዊ መሆን ግን አልቻለም።

በየአመቱ የሚገኘው 60 ሚሊየን ዶላርም የርሳቸው ዘመዶች ንብረት ለሆነው ፈርስት ኮንሰልታንሲ በአማካሪነት ስም እየባከነ መሆኑ ታውቋል።

ፈርስት ኮንሰልታንሲ በቀድሞው የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ አህመድ ቄሎና በልጃቸው ነቢል ቄሎ የሚመራ የቤተሰብ ተቋም እንደሆነ ለማወቅ ተችሏል።

በአሜሪካው ዜጋ በአቶ ካሊድ ቦምባ የሚመራው የግብርና ማበልጸጊያ ተቋም በ2008 ባሳተመው አመታዊ መጽሄት በመስኩ በአለም አቀፍ ድጋፍ ምን ተሰራ የሚለውን ከመመለስ ይልቅ የመጽሄቱን የመጀመሪያ ገጾች የሀገሪቱን ባለስልጣናት መልዕክት በማስተናገድና ስለ ሀገሪቱ የግብርና ታሪክ በመዘርዘር እንዲሁም እቅዶችን በማብራራት ወደ 130 ገጽ በሚሆነው መጽሔት የተሰራ ስራ ማስፈር አለመቻሉን ከመጽሄቱ ጋር አያይዘው ለኢሳት የደረሱት መረጃዎች አመልክተዋል።

በአጠቃላይ በ26 አለም አቀፍና አህጉራዊ እንዲሁም ሀገራዊና ግለሰባዊ ድርጅቶች ድጋፍ የሚደረግለትና በአቶ ካሊድ ቦምባ የሚመራው የግብርና ትራንስፎርሜሽን ድርጅት የታሰበለት አላማ መክሸፉን ምንጮቹ ይናገራሉ።

ሆኖም የሚመጣውን ገንዘብ የሚጠቀሙት አማካሪዎች ሀሴት እያጋበሱ መሆኑንም መረዳት ተችሏል።

የግብርና ትራንስፎርሜሽን ድርጅት ሃላፊዎች ከመንግስት ባለስልጣናት በይበልጥም ከሕወሃት ሰዎች ጋር በፈጠሩት ቅርበት ከመቀሌ ዩኒቨርስቲና ከሬዲዮ ፋና ጋር በትብብር የሚሰሩዋቸው ስራዎች በመኖራቸው የመንግስትን ከለላ ለማግኘት እንደረዳቸው የኢሳት ምንጮች ገልጸዋል።

ለጸረ ሙስና ኮሚሽን በቀረበ ሪፖርት መሰረት ጸረ ሙስና ኮሚሽን የጀመረው ምርመራ የቆመው በሕወሃት መሪዎች ግፊትና በአቶ ሃይለማርያም ደብዳቤ መሆኑን ምንጮቹ ገልጸዋል።