በቡራዩና አካባቢው የተፈጸመው ጥቃት የተቀነባበረ ነው

(ኢሳት ዲሲ–መስከረም 7/2011) በቡራዩና አካባቢው በሰላማዊ ሰዎች ላይ የተፈጸመው ጥቃት የተቀነባበረና በአንድ እዝ ስር ያረፈ መሆኑን የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽነሩ ገለጹ።

የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽነሩ ዘይኑ ጀማል ዛሬ አዲስ አበባ ላይ ለመገናኛ ብዙሃን በሰጡት መግለጫ ሁለ የፖለቲካ ድርጅቶች እጃቸው እንዳለበት ገልጸዋል።

እነዚህ ሃይሎች በአንድ ዕዝ ስር ያቀነባበሩት ጥቃት ነው ብለዋል።

የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽነሩ ጥቃት አቀናባሪዎቹ የፖለቲካ ድርጅቶች የትኞቹ እንደሆኑ በስም ከመግለጽ ግን ተቆጥበዋል።

ጥቃቱን በማድረስ የተጠረጠሩ በአዲስ አበባና በኦሮሚያ ክልል 700 የሚደርሱ ሰዎች መታሰራቸውንም ገልጸዋል።

ይህ በእንዲህ እንዳለም በቡራዩና አካባቢው የተፈጸመው ጥቃት በዋናነት በወንዶች ላይ ያነጣጠረ ሴቶችንም የጨመረ መሆኑን በአዲስ አበባ የኢሳት ሪፖርተር ያነጋገራቸው ተፈናቃዮች ገልጸዋል።

የኦሮሞ ተወላጅ የሆኑት ጎረቤቶቼ ሕይወቴን አተረፉልኝ ያሉት ተፈናቃይ የነበረውን ሁኔታ አሰቃቂ ሲሉ ገልጸውታል።

ይህ ጥቃት የመጀመሪያው አልነበረም አምናም ተመሳሳይ ሁኔታ ገጥሞን ነበር ከሚሉት ተፈናቃዮች ውስጥ አንዱ በጥቃቱ እህቱና ወንድሞቹ መገደላቸውን ገልጿል።