በሳዉዲ መካ ኢትዮጵያዉያንን ጨምሮ ያለፈቃድ ከሚገባቸዉ ጊዜ በላይ ሲኖሩ የተገኙ 85 ሰዎች በቁጥጥር ስር ዋሉ

ጥር 2 ቀን 2004 ዓ/ም

ኢሳት ዜና:-የኢትዮጵያ፡ የየመን እና የህንድን ፓስፖርት የያዙ  በሳዉዲ አረቢያ የሄዱበትን የሃጅና ኡምራ የፀሎት ጉዞ ካጠናቀቁ በሁዋላ ያለፈቃድ በመኖራቸዉ 85 ሰዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸዉን አረብ ኒዉስ ገለፀ።

ግለሰቦቹ በህገ ወጥ መንገድ በኮንስትራክሽንና በሌሎች የጉልበት የስራ መስኮች የተሰማሩ እንደነበር ሌተና ኮሎኔል ሙሃመድ አል ሁሴን የመካ ፓስፖርት ፖሊስ ሃላፊ ገልፀዋል።

በማእከላዊ ዞን ዉስጥ አጅያድ፤ ሬኦ፤ ካድዋ በተባሉት አካባቢዎች በተደረገዉ የተጠናከረ አሰሳ የተያዙትን ሰዎች ተከትሎ በሌሎችም አጎራባች አካባቢዎች የሚገኙ በህገ ወጥ መንገድ የሚኖሩ ሰዎችን የማሰሱ ሁኔታ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የገለፁት የፖሊስ አዛዥ የአገሪቱ ዜጎችና የዉጭ አገር ነዋሪዎች ያለፈቃድ የሚኖሩ ሰዎችን የሚቀጥሩና አስጠግተዉ  የሚያኖሩ ከሆነ በወንጀል እንደሚጠየቁ አስጠንቅቀዋል።

በሌላ በኩል በሳዉዲ ራፍሃ በተባለዉ አካባቢ ነዋሪ የሆነች አንዲት ኢትዮጵያዊት የቤት ሰራተኛ ባለፈዉ እሁድ እራሷን ማጥፋቷን አል መዲናህ ጋዜጣን በመጥቀስ አረብ ኒዉስ አስታዉቋል።

ሰፖንሰሯ በሰጠዉ ጥቆማ መሰረት በስፍራዉ የደረሱት ፖሊሶች ኢትዮጵያዊቷን በአንገት ልብስ ተሰቅላ እንዳገኟት ተገልጿል። ፖሊስ የአደጋዉን መንስኤ ለመከታተል ምርመራ በማድረግ ላይ ሲሆን የሟቿ አስከሬን ራፍሃ ሆስፒታል እንዲቆይ መደረጉን በተጨማሪ ለማወቅ ተችሏል።