በሱዳን የተጀመረው ተቃውሞ መቀጠሉ ተሰማ

(ኢሳት ዲሲ–ጥር 17/2011)በሱዳን የተጀመረው ተቃውሞ በተለያዩ የሃገሪቱ ክፍሎች መቀጠሉ ተሰማ።

6ኛ ሳምንቱን የያዘው ተቃውሞ እስካሁን በዝምታ ላይ የነበሩ ከተሞችንም መቀላቀሉ ተሰምቷል።

የመንግስት የጸጥታ ሃይሎች ተቃውሞውን ተከትሎ በወሰዱት ርምጃም ሶስት ሰዎች ተገድለዋል።

ከሟቾቹ ውስጥ ሁለቱ የዩኒቨርስቲ ተማሪዎች መሆናቸውን ተቃውሞውን የሚያስተባብረው የሃኪሞች ቡድን አስታውቋል።

ከ29 አመታት በፊት በመፈንቅለ መንግስት ስልጣን የያዙት የሱዳኑ ፕሬዝዳንት ጄኔራል አህመድ አልበሽር ከስልጣን እንዲወርዱ በመጠየቅ እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር ታህሳስ 19 የተጀመረው ተቃውሞ ሌሎች አካባቢዎችንም በመቀላቀል መቀጠሉ ነው የተሰማው።

በእስካሁኑ ተቃውሞም መንግስት 30 ሰዎች መገደላቸውን ሲገልጽ፣የሰብአዊ መብት ድርጅቶች ደግሞ የሟቾቹ ቁጥር በመንግስት ከተገለጸው በእጅጉ የላቀ ነው ሲሉ ይሟገታሉ።

የነዳጅና የዳቦ ዋጋ መጨመርን ተከትሎ በሱዳን የተቀሰቀሰው ተቃውሞ ሳምንታትን ያስቆጠረ ሲሆን በሃገሪቱ ያሉ የሙያ ማህበራት በጋራ እያስተባበሩት መሆኑም ታውቋል።

በሱዳን የተለያዩ ከተሞች በሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎች አደባባይ እየወጡ የአልበሽርን ስንብት እየጠየቁ በሚገኙበት ወቅት ትውልደ ሱዳናዊው ባለጸጋ መሐመድ ኢብራሒም ተቃውሞውን ደግፈው ድምጻቸውን ማሰማታቸው ይታወሳል።

ስልጣንን በሰላም ለሚለቁ የአፍሪካ መሪዎች በአለም ላይ ከፍተኛውን ሽልማት የሚሰጡት ባለጸጋው ዶክተር መሐመድ ኢብራሒም አልበሽር ስልጣናቸውን በሰላም ከለቀቁ በአለም አቀፉ የጦር ወንጀለኞች ፍርድ ቤት የተቆረጠው የእስር ማዘዣ እንዲቀርላቸው መጠየቃቸውም አይዘነጋም።