በሱዳን ካርቱም አንድ ዶክተርንና አንድ ሕጻንን ጨምሮ ሌሎች ሰዎችም ተገደሉ

(ኢሳት ዲሲ–ጥር 10/2011) በሱዳን ካርቱም በቀጠለው ተቃውሞ ትላንት አንድ የህክምና ዶክተርንና አንድ ሕጻንን ጨምሮ ሌሎች ሰዎችም መገደላቸው ተሰማ።

ፕሬዝዳንቱ ጄኔራል ኦማር አልበሽር ላይ የተነሳው ተቃውሞ አሁንም ተጠናክሮ መቀጠሉ ነው የተሰማው።

ከተቃውሞ ጋር በተያያዘ በተገደሉት ሰዎች የቀብር ስነስርአት ላይ በተገኙ ሰዎች ላይ ተኩስ መከፈቱም ታውቋል።

እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር ከታህሳስ 19 ጀምሮ በሱዳኑ ፕሬዝዳንት ጄኔራል አልበሽር ላይ የተቀሰቀሰው ተቃውሞ የተለያዩ የሕብረተሰብ ክፍሎች፣የሕክምና ባለሙያዎችና መምህራን ጭምር እየተሳተፉበት መሆኑ ታውቋል።

ፕሬዝዳንት አልበሽር ስልጣን እንዲለቁ የሚደረገው ግፊትም ቀጥሏል።

ትውልደ ሱዳናዊው ባለጸጋ መሐመድ ኢብራሒምም ጄኔራሉ ስልጣናቸውን እንዲለቁ ጥሪ አቅርበዋል።

በምላሹም በአለም አቀፉ የጦር ወንጀለኞች ፍርድ ቤት የወጣባቸው የእስር ማዘዣ እንዲሰረዝም ጠይቀዋል።

በመፈንቅለ መንግስት ስልጣን ከያዙ የፊታችን ሰኔ 30 አመት የሚሞላቸው የሱዳኑ ፕሬዝዳንት ጄኔራል ኦማር አልበሽር ስልጣን እንዲለቁ ከሚንቀሳቀሱ የሕብረተሰብ ክፍሎች ውስጥ አንዱ የህክምና ዶክተሮች ቡድን ሲሆን አንድ የዚህ ቡድን አባል ትላንት መገደላቸውን የሱዳን ማህበር /ኤስ ፒ ኤ/ አስታውቋል።

አንድ ሕጻንም በተመሳሳይ ሕይወቱን ማጣቱን ማህበሩ ጨምሮ ገልጿል።

ከርዕሰ መዲናዋ ካርቱም በተጨማሪ በራድ ሲ ሲቲ፣በፖርት ሱዳንና በሌሎች የሱዳን ከተሞች ለወር ያህል በቀጠለው ተቃውሞ እስካሁን ከ40 በላይ ሰዎች መገደላቸውን አለም አቀፍ የሰብአዊ መብት ድርጅቶች ገልጸዋል።

አምነስቲ ኢንተርናሽናል ባለፈው ሳምንት ባወጣው መግለጫ 40 ሰዎች ተገድለው ከ1 ሺ በላይ መቁሰላቸውን ሲገልጽ መንግስት የተገደሉ 24 ሰዎች ብቻ ናቸው ሲል መግለጫ ሰጥቷል።

ትውልደ ሱዳናዊው ቢሊየነር ሞ ኢብራሒም የፕሬዝዳንት አልበሽር ከስልጣን በሰላም መልቀቅ ሃገሪቱን ከእርስ በርስ ጦርነት እንደሚታደጋት ገልጸዋል።

ይህ እንዲሆን ደግሞ በምላሹ አለም አቀፉ የጦር ወንጀለኞች ፍርድ ቤት እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ2009 የቆረጠባቸውን የእስር ዋራንት እንዲያነሳ ጠይቀዋል።