በሱዳን ሁለተኛ ወሩን ያስቆጠረው ተቃውሞ እንዲያበቃ ተጠየቀ

(ኢሳት ዲሲ–ጥር 23/2011)በሱዳን ሁለተኛ ወሩን ያስቆጠረው ተቃውሞ እንዲያበቃ የሐገሪቱ ጦር ሃይሎች ኢታማዦር ሹም አሳሰቡ።

በሌላም በኩል የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ሳዲቅ አልመሐዲ ልጅ ከተቃውሞው ጋር በተያያዘ በቁጥጥር ስር ከዋሉች በኋላ መለቀቋ ተሰምቷል።

መንግስት 30 ሰዎች እንደተገደሉ ባመነበትና የሰብአዊ መብት ድርጅቶች ከ40 በላይ ሰዎች መገደላቸውን የገለጹበት ተቃውሞ 42ኛ ቀኑን አስቆጥሯል።

በሱዳን የተጀመረው ተቃውሞ እየበረታ መቀጠሉ ያሳሰባቸው የሱዳኑ ፕሬዝዳንት ጄኔራል ኡመር አልበሽር ተቃውሞውን በውጭ ሃይሎች የሚደገፍ በማለት ያጣጣሉት ሲሆን የሃገሪቱ ጦር ሃይሎች ኢታማዦር ሹምም ሐገሪቱ ወደ አደጋ ስታመራ ዝም ብለን አንመለከትም ሲሉ ዛሬ ማሳሰቢያ ሰተዋል።

የሃገሪቱ ጦር ሃይሎች ኢታማዦር ሹም ጄኔራል ከማል አብዱልማሩፍ ሱዳን እንድትፈርስ ወይንም ወደ አልታወቀ ሁኔታ ውስጥ እንድትገባ አንፈቅድም በማለት ማሳሰቢያ ሰተዋል።

ተቃውሞውን እያስተባበሩ ያሉት አክቲቪስቶች ደግሞ ሰራዊት ከሕዝቡ ጎን ተሰልፎ የለውጥ እንቅስቃሴውን እንዲደግፍ ጥሪ አቅርበዋል።

በ46 አመታቸው ደም ባፋሰሰው መፈንቅለ መንግስት ስልጣን የያዙት የ75 አመቱ የሱዳኑ ፕሬዝዳንት ጄኔራል ኡመር አልበሽር የ29 አመታት የስልጣን ዘመናቸው እንዲያበቃ እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር ታህሳስ 19/2018 የተጀመረው ተቃውሞ የሐገሪቱን የሙያ ማህበራት በዋናነት እያሳተፈ ቀጥሏል።

የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ሳዲቅ አልመሐዲም ጄኔራል ኡመር አልበሽር ስልጣን እንዲለቁ በአደባባይ ጠይቀዋል።

የአዛውንቱ ሳድቅ አልመሐዲ ልጅ የሆነችውን አተቃዋሚው ኡማ ፓርቲ አመራር መርያም ሳዲቅ አልመሐዲ ትላንት በጸጥታ ሃይሎች ከተወሰደች በኋላ ተለቃለች።

መርያም ሳድቅ አልመሐዲ የኡማ ፓርቲ ምክትል ሊቀመንበር ስትሆን አባትዋ ሳድቅ አልመሐዲ ሊቀመንበር ሆነው ይመሩታል።

መንግስት ከመርያም በተጨማሪ አንድ ቀን ቀደም ብሎ ከተቃውሞው ጋር በተያያዘ የታሰሩ 186 እስረኞችን ለቋል።

የሰብአዊ መብት ድርጅቶች የታሰሩት ከ1ሺ በላይ ስለሆኑ ሁሉም ይለቀቁ ሲሉ ጥሪ አቅርበዋል።