በሱዳንና በኢትዮጵያ መካከል ያለው ጦርነት ቢቆምም ፍጥጫው ግን እንደቀጠለ ነው

በሱዳንና በኢትዮጵያ መካከል ያለው ጦርነት ቢቆምም ፍጥጫው ግን እንደቀጠለ ነው
(ኢሳት ዜና ሰኔ 27 ቀን 2010 ዓ/ም) ሰሞኑን የሱዳን የመከላከያ ሃይል በመተማ አካባቢ በሚገኝ የኢትዮጵያ መሬት ላይ የይገባኛል ጥያቄ ማንሳታቸውን ተከትሎ በተነሳ ጦርነት ድንበራቸውን ለማስከበር የተሰው አርሶአደሮችና የመከላከያ ሰራዊት ዛአስከሬን ዛሬ ወደ ኢትዮጵያ ገብቷል። ጦርነቱ ለጊዜው ቢቆምም ፍጥጫው ግን እንደቀጠለ ነው።
የምዕራብ ጎንደር ዞን ዋና አስተዳዳሪ የሆኑት ዘላለም ልጃለም ሱዳኖች የሚጠይቁት መሬት የኢትዮጵያ መሆኑን ገልጸው፣ ሱዳኖች በአርሶአደሮች ላይ በከፈቱት ጦርነት ግጭት መፈጠሩን ተናግረዋል። አርሶአደሮች ራሳቸውንና አገራቸውን ለመጠበቅ የመከላከል እርምጃ የወሰዱ ሲሆን፣ የመከላከያ ሰራዊትም ወደ አካባቢው በመንቀሳቀስ ጥበቃ እያደረገ ነው። በተኩስ ልውውጥ አንድ የሱዳን ሻለቃ አመራርን ጨምሮ 7 የሱዳን ወታደሮች ተገድለዋል። በኢትዮጵያ በኩል ደግሞ 3 አርሶአደሮችና 2 የመከላከያ አባላት ተሰውተዋል። 6 ሰዎች ቆስለው ሆስፒታል ገብተዋል።
የፌደራል መንግስት በአፋጣኝ ተሰብስቦ በጉዳዩ ላይ እንደሚመክርም ታውቋል። ምንጮች እንደሚገልጹት ለውጡን ለመቀልበስ የተነሱ የህወሃት ባለስልጣናት ሰሞኑን ወደ ሱዳን በመመላለስ በአማራ ክልል አካባቢዎች ጦርነት እንዲጀመር ሱዳኖችን ሲያግባቡ ሰንብተዋል። የምዕራብ ትግራይ አስተዳዳሪ የሆነው ተኬ የተባለ ሰው በሚስጢር ወደ ሱዳን አቅንቶ ከሱዳን ባለስልጣናት ጋር ተነጋግሯል። ግለሰቡ ከሱዳን ባለስልጣናት ጋር ከተነጋገረ በሁዋላ በድብቅ ወደ ቤንሻነጉል ጉሙዝ ክልል አቅንቷል።