በሰሜን ወሎ ውጥረቱ እንደቀጠለ ነው

(ኢሳት ዲሲ–ጥር 23/2010)

በሰሜን ወሎ ያለው ውጥረት መቀጠሉ ታወቀ።

በብአዴን አመራሮች የሚጠሩ ሰብሰባዎችም እየተበተኑ መሆኑ ተሰምቷል።

ከቆቦ ጀምሮ እስከ መርሳ ዛሬ መንገዶች ዝግ ናቸው።

ከቆቦ ወደ ትግራይ የሚመላለሱ ተሽከርካሪዎች በወታደሮች ታጅበው መሆኑን የደረሰን መረጃ አመልክቷል።

በወልዲያ የትግራይ ህዝብ ነጻ አውጪ ግንባር ወታደሮች በህዝቡ ላይ ግፍ እየፈጸሙ መሆናቸውን ነዋሪዎች ይናገራሉ።

ከመርሳና ወልዲያ በትንሹ 500 ወጣቶች በአፋር ጭፍራ በረሃ ተወስደው በስቃይ ላይ ናቸው ተብሏል።

ሰሜን ወሎ ከ10 ቀናት በፊት የጀመረው ህዝባዊ ተቃውሞ ውጥረቱ አልበረደም።

በርካታ መንገዶች እንደተዘጉ ናቸው። የንግድ እንቅስቃሴው እንደቆመ ነው።

በመርሳ፣ በሲሪንቃ፣ በወልዲያና በቆቦ የመንግስት መስሪያ ቤቶች መደበኛ እንቅስቃሴያቸውን መጀመር አልቻሉም። ትምህርት ቤቶችም ዝግ ናቸው።

የትግራይ ህዝብ ነጻ አውጪ ግንባር ባሰማራቸው የብአዴን አመራሮች የተጠሩት ስብሰባዎች ዓላማቸው በየከተሞቹ ያለውን የሰላም መደፍረስ ለመቅረፍ እንደሆነ ቢገለጽም በአብዛኞቹ ከተሞች በህዝብ ተቃውሞ ስብሰባዎቹ መጨናገፋቸውን የደረሰን መረጃ አመልክቷል።

በቆቦ አቶ አለምነው መኮንን ከፍተኛ ተቃውሞ ገጥሟቸው ስብሰባው ሲበተን፣ በመርሳ የሀገር ሽማግሌዎች ከብአዴን አመራሮች ጋር ያለስምምነት መለያየታቸው ታውቋል።

ከወልዲያ የሚወጡ መረጃዎች እንደሚያመለክቱት የትግራይ ህዝብ ነጻ አውጪ ግንባር ህውሃት በህዝቡ ላይ ከፍተኛ ስቃይና ግፍ በመፈጸም ላይ ነው።

የአጋዚ ወታደሮቹን ያሰማራው የትግራይ ነጻ አውጪ ግንባር ህወሃት ቤት ለቤት በመሄድ ህጻናትን፣ እናቶችን፣ ነፍሰ ጡሮችን ሳይቀር በመደብደብ ላይ መሆኑን ለማወቅ ተችሏል።

ወጣቶችን በወላጆቻቸው ፊት በጉልበታቸው ተንበርክከው በኮብል ስቶን ላይ እንዲራመዱ በማድረግ የጭካኔ ተግባር በመፈጸም ላይ መሆኑን ኢሳት ያነጋገራቸው ነዋሪዎች ገልጸዋል።

ማንኛውም ወጣት መንገድ ላይ ከታየ እንደሚደበደብና እንደሚታሰር የገለጹት ነዋሪዎች ቢያንስ 300 የሚሆኑ የወልዲያ ወጣቶች ታፍሰው ወደ አፋር ክልል ጭፍራ መወሰዳቸውን ጠቅሰዋል።

የብአዴን አመራሮች በየስብሰባው ለሀገር ሽማግሌዎች የሚታሰር እንደማይኖር ቃል ቢገቡም የትግራይ ህዝብ ነጻ አውጪ ግንባር ወጣቶችን በገፍ ማሰር መቀጠሉን ነዋሪዎች ይናገራሉ።

ብአዴኖች እስረኞችን የማስፈታት አቅም እንደሌላቸውና ውሳኔው የትግራይ ነጻ አውጪ ግንባር አመራሮች እንደሆነም መረጃዎች አመልክተዋል።

በመርሳ ያለው ሁኔታም አስጊ እንደሆነ ከአገዛዙ ጋር ቅርበት ያላቸው መገናኛ ብዙሃን ሳይቀር እየገለጹ ናቸው።

በማንኛውም ሰዓት አመጽ ሊፈነዳ የሚችል እንደሆነም ይነገራል።

በመርሳ ዛሬም መረጋጋት የለም። ንግድ ቦታዎች ስራ አልጀመሩም።

ወጣቱ እየታፈሰ ሲሆን ከ200 በላይ የሚሆኑት ወደ አፋር ጭፍራ ተወስደዋል ሲሉ የኢሳት ምንጮች ገልጸዋል።

በጭፍራ በረሃ በሚገኘው እስር ቤት በርካታ ወጣቶች በትግራይ ህዝብ ነጻ አውጪ ግንባር አማካኝነት ከፍተኛ ድብደባና ስቃይ እየተፈጸመባቸው መሆኑንም ለማወቅ ተችሏል።

በሌላ በኩል በሰሜን ወሎ አብዛኞቹ መንገዶች በመዘጋታቸው ወደ ትግራይ የሚጓጓዙ ተሽከርካሪዎች በወታደራዊ አጀብ መሆኑን ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

በተለይ አትክልትና ፍራፍሬ ጭነው ከቆቦ ዙሪያ ወደ ትግራይ የሚገቡ ተሽከርካሪዎች በአጋዚ ወታደሮች ካልታጀቡ በቀር አይንቀሳቀሱም ብለዋል የኢሳት ምንጮች።