በሰሜን ሸዋ ዞን ችግር ተፈጥሮባቸው የነበሩት አካባቢዎች እየተረጋጉ ነው

(ኢሳት ዲሲ–ሚያዚያ 2/2011)አማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን ሰሞኑን ችግር ተፈጥሮባቸው የነበሩት አካባቢዎች እየተረጋጉ መሆኑን የክልሉ የሰላም ግንባታና የህዝብ ደህንነት ጉዳዮች ቢሮ ምክትል ሃላፊ ገለጹ።


ምክትል ሃላፊው አቶ ገደቡ ሃይሉ እንደሚሉት በአካባቢዎቹ ዳግም ችግሮች እንዳይፈጠሩ የመከላከያ፣የክልሉ ልዩ ሃይልና ሰላም አስከባዊ ሃይሉ በጋራ በመስራት ላይ ናቸው።
በአካባቢው ልዩ ኮማንድ ፖስትን ለማቋቋም ወደ አካባቢው የተላከ የክልሉ የጸጥታ ሃይል መኖሩንም ገልጸዋል።
በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን በተለይ አበጣዬና በማጀቴ የታጠቁ ሃይሎች ባደርሱት ጥቃት ከ20 በላይ የሚሆኑ ሰዎች ሕይወታቸው አልፏል፣ቁጥራቸው እስካሁን መረጋገጥ ያልቻለ ሰዎች ደግሞ ቆስለዋል።
በንብረት ደረጃም ከባድ ውድመት ደርሷል ይላሉ የክልሉ የሰላም ግንባታና የህዝብ ደህንነት ጉዳዮች ምክትል ሃላፊ አቶ ገደቤ ሃይሉ።
አሁን ላይ አካባቢው ወደ ተረጋጋ ሁኔታ እየተመለሰ መሆኑንና ለዚህም የመከላከያና የክልሉ ጸጥታ ሃይል የትብብር ስራ መስራታቸውን ነው የተናገሩት።
አካባቢውን ከማረጋጋት ባለፈም ሕይወታቸውን ለማዳን ሲሉ ወደ ተለያዩ አካባቢዎች የሸሹ ነዋሪዎችንም ወደ ቀያቸው የመመለሱ ስራ እየተከናወነ ነው ብለዋል።
በቀጣይም እንዲህ አይነቱ ጥቃት እንዳይፈጸም በክልል ደረጃ የተቀመጠ ቀጣይ ስራ አለ ሲሉ ገልጸዋል።–የክልሉን ህዝብ ከማንኛውም መጠበቅና ችግር በተፈጠረባቸው አካባቢዎች ኮማንድ ፖስት ማቋቋምን በማሳያነት በማቅረብ።
ምክትል ሃላፊው አቶ ገደቤ እንደሚሉት የጸጥታ ሃይሉም ሆነ የማንኛውም አካል ቅድሚያ ተግባር የዜጎችን ሰላም ማስከበር ነው።
ወደ አካባቢው የተላከው የጸጥታ ቡድንም የአካባቢውን ሰላም የሚያስከብር ኮማንድ ፖስት ያቋቁማል ብለዋል።
ጥቃት ስለፈጸመውም አካል ቢሆን ወደ ፊት መረጃ የምንሰጥ ቢሆንም አሁን ላይም የታዘብንውና ያየንው ነገር አለ ብለዋል አቶ ገደቤ።