በምዕራብ ጎንደር 138 ግለሰቦች በተለያዩ ወንጀሎች ተጠርጥረው ታሰሩ

(ኢሳት ዲሲ–የካቲት 15/2011)በምዕራብ ጎንደር ዞን ካለው ግጭት ጋር በተያያዘ 138 ግለሰቦች በሕይወት ማጥፋትና በተለያዩ ወንጀሎች ተጠርጥረው መታሰራቸው ተነገረ።

በግጭቱ ሳቢያ 37 ሰዎች በነፍስ ግድያ፣ 101 ግለሰቦች ደግሞ በስርቆትና በሌሎች ወንጀሎች ተጠርጥረው በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን የ33ኛ ዓባይ ክፍለ ጦር አስታውቋል ።

በምዕራብ ጎንደር  ግጭት ጥቅም ላይ ሲውሉ የነበሩ የቡድን የጦር መሣሪያ ጥይቶችና መሳሪያዎች  መያዛቸውም ተነግሯል።

በምዕራብ ጎንደር ዞን ካለው ግጭት ጋር በተያያዘ 138 ግለሰቦች በነፍስ ግድያና በተለያዩ ወንጀሎች ተጠርጥረው የተያዙት በመከላከያ ሰራዊት አባላት ነው።

ጥይቶቹ የተያዙትማ በመተማ ዮሐንስ ከተማ በተቃጠሉ ግለሰቦች ቤት ውስጥ መሆኑን የ33ኛ ዓባይ ክፍለ ጦር 1ኛ ብርጌድ 1ኛ ሻለቃ አዛዥ ሌተናል ኮሎኔል አንገሶም አርአያ ተናግረዋል ።

ከጦር መሳሪያ ጥይቶቹ በተጨማሪ ሃሰተኛ የብር ኖቶች፣ አደንዛዥ ዕፆች፣ የቅስቀሳ መሣሪያዎች (ድምጽ ማጉያ) እና የተለያዩ ሰነዶች በቁጥጥር ስር ውለዋል ነው ያሉት ።

ከዚህ ባለፈም የእጅ ቦንብም፣ የቅንቡላ፣ የአርፒጂ (የላውንቸር) እና የብሬንና ጥይቶችም በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ሌተናል ኮሎኔል አንገሶም አንስተዋል።

በቁጥጥር ስር የዋሉት የጦር መሳሪያ ጥይቶችን ለታንክ እና ለከባድ ምሽግ ማጥቂያ የሚያገለግሉ ሆነው ለሃገር መከላከያ ሠራዊት እና ለተፈቀደላቸው የፀጥታ አካላት ብቻ የሚፈቀዱ እንደሆኑም ገልጸዋል፡፡

ክላሽ፣ ሽጉጦች፣ ስለታማ መሣሪያዎች፣ የፌዴራል ፖሊስና የሀገር መከላከያ የደንብ ልብሶችም በተቃጠሉ ቤቶች ውስጥ መገኘታቸውንም  ሌተናል ኮሎኔሉ አረጋግጠዋል።

አሁን የተገኙት የቡድን መሣሪያዎቹ ጥይቶች ናቸውም ብለዋል።

አሁንም ተጨማሪ የጦር መሳሪያዎች በግለሰቦቹ እጅ እንዳሉ እንደሚታመን ጠቁመዋል።

በምዕራብ ጎንደር የህብረተሰቡን ሰላም ለመጠበቅ መከላከያ ሰራዊት ከክልሉ ፖሊስና ከአካባቢው የፀጥታ አካላት ጋር  ተቀናጅቶ እየሠራ መሆኑን ነው የገለጹት።

ተጠርጣሪ ግለሰቦች በቁጥጥር በሚውሉበት ጊዜ መንግሥት በቶሎ ለህግ እያቀረበ አለመሆኑን የአማራ መገናኛ ብዙሃን ዘግቧል ።