በምዕራብ ጎንደር ሰላማዊ ዜጎች የተገደሉበት ግጭት እየተመረመረ ነው ተባለ

(ኢሳት ዲሲ–ጥር 2/2011)በምዕራብ ጎንደር ዞን ሰላማዊ ዜጎች የተገደሉበትን ግጭት እየመረመረው መሆኑን የአማራ ክልል መንግስት አስታወቀ።

የክልሉ የሰላምና ደህንነት ቢሮ ሃላፊ ብርጋዴር ጄነራል አሳምነው ጽጌ ለኢሳት እንደገለጹት በመከላከያ ሰራዊቱ የተወሰደውን ርምጃ በተመለከተ የክልሉ መንግስት ከሚመለከታቸው የፌደራል መንግስት አካል ጋር እየተነጋገረ ነው።

በአንዳንድ አካባቢዎች ግጭቶች ዛሬ መቀጠላቸውን ብርጋዴር ጄነራል አሳምነው ጽጌ ገልጸዋል።

በሌላ በኩል የአማራ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ አዴፓ ማዕከላዊ ኮሚቴ ባወጣው አጭር መግለጫ ጉዳዮ ተጣርቶ አጥፊዎቹን ለህግ ለማቅረብ የሚያስችል አጣሪ ግብረ ሃይል ተቋቁሞ ወደ ስፍራዉ መንቀሳቀሱን ገልጿል።

ብርጋዴር ጄነራል አሳምነው ጽጌ የግጭቱ መነሻ በህዝቡ ጥያቄ በፍርድ ቤት ማዘዣ ጭምር የተደገፈውን የፍተሻ ጥያቄ ሱር ኮንስትራክሽን አልቀበልም ማለቱ  እንደሆነ ይገልጻሉ።

ህብረተሰቡ ጥርጣሬ አለኝ ማለቱን የጠቀሱት ብርጋዴር ጄነራል አሳምነው ጽጌ የፍርድ ቤትን ትዕዛዝ ወደጎን በመተው ንብረቱን ይዞ ለመውጣት በሞከረው የሱር ኮንስትራክሽን ድርጅት ላይ ተቃውሞ መነሳቱን ገልጸዋል።

በክልሉ በሚከናወኑ የጸጥታ ጉዳዮች ላይ ጥበቃ ማድረግ ካስፈለገም የክልሉ ፖሊስ እያለ መከላከያ ስራውን ማከናወኑ ተገቢ አልነበረም ያሉት ብርጋዴር ጄነራል አሳምነው ጽጌ የበላይ አካላት ጉዳዩን ስለማወቃቸው እርግጠኛ አይደለሁም እያጣራነው እንገኛለን ብለዋል።

በመከላከያ ሰራዊቱ የአካባቢው ምድብ በተወሰደው በዚሁ ርምጃ ስድስት ሰዎች መገደላቸውንና 18 መቁሰላቸውን የገለጹት ብርጋዴር ጄነራል አሳምነው ጽጌ አንዲት ህጻን ከተገደሉት መካከል ትገኛለች ብለዋል።

ክላሽ በያዘ ህዝብ ላይ ከባድ መሳሪያ የታጠቀው መከላከያ ሰራዊት የወሰደው ርምጃ ተገቢ አይደለም ሲሉም ኮንነዋል።

የመከላከያ ምክትል ኤታ ማዦር ሹም ጄነራል ብርሃኑ ጁላ መከላከያ ሰራዊቱ ስለተተኮሰበት ራሱን ለመከላከል የወሰደው ርምጃ ነው ማለታቸውን በተመለከተ የተጠየቁት የአማራ ክልል የሰላምና ደህንነት ቢሮ ሃላፊ ብርጋዴር ጄነራል አሳምነው ጽጌ ይህን ያህል ጉዳት ሰላማዊ ዜጎች ላይ ርምጃ የሚያስወስድ ነገር የለም፡፡

አርሶ አደሩ ቢተኩስ እንኳን በመከላከያ የተወሰደው አጸፋ ተገቢነት የለውም ሲሉ ገልጸዋል።

የአማራ ክልል መንግስት ጉዳዩን በትኩረት እየተመለከተው እንደሆነ ብርጋዴር ጄኔራል አሳምነው ጽጌ ገልጸዋል።

የአካባቢውን ጸጥታ ከማስከበር አንስቶ የምርመራ ስራ እንደሚያከናውኑም ገልጸዋል።

ግጭቱ ሌላ መልክ እንዲይዝ የሚፈልጉና የአረዳድ ልዩነት ካላቸው አካላት ጭምር ውይይት እንደሚደረግ የገለጹት ብርጋዴር ጄነራል አሳምነው ጽጌ በመከላከያ ሰራዊት የአካባቢው ምድብ ውስጥ ያለውን አድሎአዊና አንድን ወገን ለይቶ የሚደረግ ጥቃትን በተመለከተ ከበላይ አካላት ጋር በመነጋገር ላይ መሆናቸውን አስረድተዋል።

በዛሬው ዕለትም በአንዳንድ አካባቢዎች ግጭቶች መኖራቸውንም ገልጸዋል።

በሌላ በኩል የክልል ገዢ ፓርቲ አዴፓ ማዕከላዊ ኮሚቴ አጣሪ ግብረ ሃይል ወደ አካባቢው መላኩን አስታውቋል።

ጉዳዩ ተጣርቶ አጥፊው ወገን ለህግ እንደሚቀርብም አዴፓ ገልጿል።

ዝርዝር ጉዳዩ ለዚህ ዘገባ መድረስ ባይችልም የአማራ ክልላዊ መንግስት ፕሬዝዳንት አቶ ገዱ አንዳርጋቸው በወቅታዊ ጉዳይ ላይ መግለጫ መስጠታቸው ታውቋል።