በምዕራብ ጉጂ 33 ትምህርት ቤቶች ስራ ጀመሩ

(ኢሳት ዲሲ–ጥር 10/2011)በኦሮሚያ ክልል በምዕራብ ጉጂ ዞን በፀጥታ ችግር ተዘግተው የነበሩ 33 ትምህርት ቤቶች ወደ ስራ መመለሳቸው ተነገረ።

በአካባቢው ተፈጥሮ የነበረው የፀጥታ ችግር ተሻሽሎ አንጻራዊ ሰላም መስፈኑንም የምዕራብ ጉጂ  ዋና አስተዳዳሪ መግለጻቸው ተዘግቧል።

ፋይል

ይሕ በእንዲህ እንዳለ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ካማሺ ዞን በንፁሃን ዜጎች ላይ ወንጀል የፈፀሙ 60 ሰዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸው ተነግሯል።

በኦሮሚያ ክልል ጉጂ ዞን ተከስቶ የነበረው የፀጥታ ችግር በማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ  ሲፈጥር ቆይቷል።

ችግሩን ለመፍታት አስተዳደሩ በአባገዳዎች ሰብሳቢነት  ከኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) አባላት ጋር በመወያየት በአሁኑ ወቅት በአካባቢው አንጻራዊ ሰላም መስፈኑ ነው የሚነገረው።

እናም በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ጉጂ ዞን በፀጥታ ችግር ተዘግተው የነበሩ 33 ትምህርት ቤቶች ማስተማር መጀመራቸው ታወቋል።

በምዕራብ ወለጋና ምዕራብ ጉጂ የኦነግ ታጣቂዎች እየፈጸሙ በነበረው ጥቃት መንግስት ችግሩን በሰላም ለመፍታት ሲታገስ ቢቆይም ችግሩ እየተባባሰ ሲመጣ የሃይል ርምጃ መውሰድ በመጀመሩ አካባቢው በአንጻራዊነት  እየተረጋጋ መቷል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ካማሺ ዞን በንፁሃን ዜጎች ላይ ወንጀል ፈጽመዋል የተባሉ 60 ሰዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸው ተነግሯል።

የኦሮሚያ ክልል የመንግስት ኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ እንደገለጸው ተጠርጣሪዎቹ በቁጥጥር ስር የዋሉት የምዕራብ ኢትዮጵያ ኮማንድ ፖስት ከክልሎች ጋር በቅንጅት ባከናወነው ስራ ነው።

በተጠርጣሪዎቹ እጅ የነበሩ የተለያዩ የጦር መሳሪያዎችም በቁጥጥር ስር መዋላቸውም ታውቋል።

በቁጥጥር ስር የዋሉ የጦር መሳሪያዎችም 2 ብሬይን፣ 27 ክላሽንኮቭ፣ 140 ኋላቀር የጦር መሳሪያዎች፣ 4 የእጅ ቦምብ፣ 5 ሽጉጥ እና 87 የተለያዩ ጥይቶች ናቸው ተብሏል።

አሰቃቂ ወንጀል ሲፈፀምባቸው የነበሩ 261 ቀስቶችም በቁጥጥር ስር ውለዋል ።