በምዕራብ ጉጂ ኦሮሚያ ለተፈናቀሉ ዜጎች የ118 ሚሊየን ዶላር እርዳታ ተጠየቀ

(ኢሳት ዲሲ–ሐምሌ 5/2010) በምዕራብ ጉጂ ኦሮሚያ ለተፈናቀሉ 1 ሚሊየን ለሚጠጉ ሰዎች የ118 ሚሊየን ዶላር እርዳታ መንግስት ጠየቀ።

የኢትዮጵያ መንግስት አለምአቀፍ እርዳታውን የጠየቀው በአካባቢው ለተፈናቀሉ ሰዎች የምግብ፣የመጠጥና ለልዩ ልዩ እርዳታ የገንዘብ እጥረት ስለገጠመው መሆኑ ተነግሯል።

የአደጋና ዝግጁነት ኮሚሽን በጌዲዮ ለተፈናቀሉ ሰዎች እስካሁን 7 ሚሊየን ዶላር የእርዳታ ገንዘብ ብቻ እንዳለው አስታውቋል።

በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ጉጂ ዞን ከማንነት ጋር በተያያዘ ከ1 ሚሊየን የሚበልጡ የጌዲዮ ተወላጆች ተፈናቅለዋል።

በመቶ የሚቆጠሩ ሰዎች የተገደሉበት ይሄው ግጭት ለበርካታ ሕጻናት፣ሴቶችና አረጋውያን መፈናቀል ምክንያት ሆኗል።

በግጭቱ ቤቶች ተቃጥለዋል ንብረቶች ወድመዋል።

በአካባቢው ከባድ የምግብ እጥረት መከሰቱም ተገልጿል።

በዚህ ሁኔታ የደረሰውን ሰብአዊ ቀውስ ለመታደግ ደግሞ መንግስት ከአቅሙ በላይ እንደሆነበትም ሊቋቋመው አልቻለም ተብሏል።

የመንግስት እርዳታ አነስተኛ ነው በተባለበት በዚህ የጌዲዮ ቀውስ አለም አቀፍ ለጋሾች ጣልቃ መግባታቸው ይታወቃል።

ይህም ሆኖ ግን ቁጥራቸው 1 ሚሊየን ያህል ለሚሆኑት ተፈናቃዮች በአግባቡ ለመርዳት አሁንም የገንዘብ እጥረት እንዳለ ተገልጿል።

የብሔራዊ አደጋ መከላከል ኮሚሽን እንዳስታወቀው በምዕራብ ጉጂ ዞን ለሚያስፈልገው የእርዳታ ስራ 118 ሚሊየን ዶላር ገንዘብ ተግባር ላይ መዋል አለበት።

እናም ለዚሁ እርዳታ አለምአቀፍ ለጋሾች ገንዘቡን እንዲሰጡ ጥሪ አቅርቧል።

እንደ ኮሚሽኑ ገለጻ ለምግብ ብቻ 62 ነጥብ 3 ሚሊየን ዶላር ያስፈልጋል።

ለውሃና ለንጽህና ደግሞ 20 ነጥብ 5 ሚሊየን ዶላር ያስፈልጋል ነው የተባለው።

እስካሁን ባለው ሁኔታ አየርላንድ 1 ነጥብ 8 ሚሊየን ዶላር ስትለግስ ሲውዲን ደግሞ 2 ነጥብ 3 ሚሊየን ዶላር እሰጣለሁ ብላለች።–ከዚህ ውጪ የተለገሰ ገንዘብ እንደሌለ ነው የተነገረው።

በኮሜሽኑ ገለጻ መሰረት ለጌዲዮ ተፈናቃዮች የሚሆን የ7 ሚሊየን ዶላር ክምችት ብቻ ይገኛል።

እናም አለም አቀፍ ለጋሾች 118 ሚሊየን ዶላር ካልሰጡ ቀውሱ ተባብሶ እንደሚቀጥልና ብዙ ሰዎች ሊጎዱ እንደሚችሉም የአዲስ ፎርቹን ዘገባ አመልክቷል።