በምንጃር ሾንኮራ ህዝባዊ አመጽ ተቀሰቀሰ

(ኢሳት ዜና–ጥቅምት 29/2010)በሰሜን ሸዋ ምንጃር ሾንኮራ ህዝባዊ አመጽ ተቀሰቀሰ።–በጨፌ ዶንሳ ትላንት የጀመረው ተቃውሞም ተባብሶ መቀጠሉ ታውቋል።

የምንጃር ሸንኮራ ህዝብም የቻይና ቺፑድ ፋብሪካን በማቃጠል ማውደሙ ተገልጿል።

የአማራ ወጣቶችና የኦሮሞ ቄሮዎች በጋራ እየሰሩ መሆኑን ለኢሳት የደረሰው መረጃ አመልክቷል።

በሌላ በኩል በሰሜን ጎንደር ወገራ አንድ የሚሊሺያ ሃላፊ በነጻነት ሃይሎች ታፎኖ መወሰዱ ተሰምቷል።

ምንጃር ሸንኮራ ህዝባዊ አመጹ የተጀመረው ዛሬ ነው። ለ15 ቀናት መብራት ያላገኘው ህዝብ ወደ አደባባይ ወጥቶ ምሬቱን ለመግለጽ ከበቂ በላይ ምክንያት ነበረው።

ባለፉት 26 ዓመታት በህዝባዊ ወያኔ ሀርነት ትግራይ በተለየ ሁኔታ ግፍና መከራ የደረሰበት አከባቢ ነው ሰሜን ሸዋ።

ባለፉት ሁለት ዓመታት በአማራና በኦሮሚያ የተቀጣጠለው ህዝባዊ እምቢተኝነት ሰሜን ሸዋ መድረሱ የማይቀር እንደነበር ምልክቶች መታየት ከጀመሩ ቆይተዋል።

ለሁለት ሳምንት መብራት ሲያጣ የሚታገሰው አልነበረም። ፈንቅሎ ወጣ። በአቅራቢያ በሚገኘው ጨፌ ዶንሳ ከተማ የተጀመረው ተቃውሞን የምንጃር ሾንኮራ ህዝብ ዛሬ ተቀላቀለው።

ዛሬ አደባባይ የወጣው የምንጃር ሾንኮራ ህዝብ የተጠራቀመውን ብሶትና ቁጣ የገለጸው በተለይ የመንግስት መስሪያ ቤቶች ላይ ጥቃት በመሰንዘር ነው።

ምንጃርና ጨፌ ዶንሳ አንድ ላይ ተነሱ። የአማራና የኦሮሞ ልጆች ስለአንድ ዓላማ ድምጻቸውን ለማሰማት አደባባይ መውጣታቸውን ነው ከአካባቢው ኢሳት ያነጋገራቸው የገለጹት።

በምንጃር ሾንኮራ እየተካሄደ ባለው ህዝባዊ ተቃውሞ የተለያዩ የመንግስት መስሪያ ቤቶች ላይ ጥቃት ተፈጽሟል።

የወረዳ ካቢኔዎች መኖሪያ ቤቶች ላይም ጥቃት የተፈጸመ ሲሆን አብዛኞቹ ቤቶች መፈራረሳቸው ተገልጿል።

በከተማዋ በሚገኘውና በቻይናውያን ንብረትነት የሚታወቀውን የቺፑድ ፋብሪካ በእሳት በማያያዝ እንዲወድም የተደረገ ሲሆን የፋብሪካው ሰራተኞች ተኩስ ከፍተው ሁለት ወጣቶችን ማቁሰላቸው ታውቋል።

በጨፌ ዶንሳ ከተማ የሚገኙ ቄሮዎች ለሁለተኛ ቀን ከፍተኛ ህዝባዊ ተቃውሞ እያደረጉ ነው።

ከሸንኮራ ምንጃር ወጣቶች ጋር በመደዋወልና በመነጋገር ተቃውሞውን አጠናክረው ቀጥለዋል።

የኦህዴድ ጽ/ቤትን ጨምሮ በርካታ ድርጅቶች ወድመዋል። የመከላከያና የፌደራል ፖሊስ በህዝቡ ላይ ተኩስ መክፈታቸውም ታውቋል።

የቻይና አረርቲ ኢንዱስትሪ ፓርክም ከፍተኛ ወድመት ደርሶበታል። የአረርቲ ኢንዱስትሪ ፓርክ ሃላፊዎች ወታደሮች እንዲላኩላቸው ጥያቄ ቢያቀርብም ከመንግስት በኩል የተሰጠ መልስ እንዳልነበረ ለማወቅ ተችሏል።

የቻይና ዜጎችን ለማስወጣት ተሽከርካሪዎች የተንቀሳቀሱ ሲሆን ይህ ዘገባ እስከተጠናቀረበት ጊዜ ድረስ የቻይና ዜጎች ስለመውጣታቸው የታወቀ ነገር የለም።

በጨፌ ዶንሳ የመንግስት አመራሮች በአብዛኛው ለስብሰባ መቀሌ መሆናቸው የተገለጸ ሲሆን ህዝቡ ከተማዋን ተቆጣጥሮ እስክምሽት ድረስ ተቃውሞውን በማሰማት መቀጠሉን የደረሰን መረጃ አመልክቷል።

በአማራና በኦሮሞ ወጣቶች ቅንጅት በምንጃር ሸንኮራና ጨፌ ዶንሳ እየተካሄደ ያለው ጸረ መንግስት ተቃውሞ በአስቸኳይ የህወሀት ስርዓት ከስልጣን እንዲወርድ የሚጠይቅ እንደሆነም ተገልጿል።

በሌላ በኩል በሰሜን ጎንደር ዞን ወገራ ህዝቡን ትጥቅ ለማስፈታት ዘመቻ ተሰጥቶት የተሰማራ አንድ የሚሊሺያ አመራር በነጻነት ሃይሎች ተማርኮ ወደ በረሃ እንደተወሰደ ከአካባቢው የደረሰን መረጃ አመልክቷል።

የሚሊሺያ አመራሩ ከነትጥቁ ታፍኖ ወደ በረሃ ከመወሰዱ በፊት ከነጻነት ሃይሎች ጋር የተኩስ ልውውጥ ያደረገ ሲሆን ረዳቱ ሲቆስል አመራሩ ግን መማረኩ ነው የተገለጸው። የቆሰለው ረዳት ሚሊሺያ ደባርቅ ሆስፒታል መግባቱም ታውቋል።