በሜቴክ ሳቢያ የ36 ሚሊየን ዶላር ኪሳራ አስከተለ

(ኢሳት ዲሲ–ህዳር 12/2011)የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ሃይል ኮርፖሬሽን በአፋር ክልል እገነባዋለሁ በማለት የተንቀሳቀሰበት የእንፋሎት ሃይል ማመንጫ ፕሮጀክት በሜቴክ ሳቢያ የ36 ሚሊየን ዶላር ኪሳራ ማስከተሉ ተገለጸ።

በጄኔራል ክንፈ ዳኘው ይመራ የነበረው ሜቴክ ከኮንትራት ስምምነቱ ውጪ ከውጭ ያስገባቸው መሳሪያዎች አሮጌዎችና ያልተሟሉ በመሆናቸው ለፕሮጀክቱ መክሸፍና ለተከተለው ኪሳራ ምክንያት እንደሆነም መረዳት ተችሏል።

137 ሜጋ ዋት ያመነጫል የተባለው የሃይል ማመንጫ ፕሮጀክትም መክሸፉ ተመልክቷል።

ሒደቱን በቅርብ ሲከታተሉ የነበሩ ምንጮች ለኢሳት እንደገለጹት በአፋር ክልል አዋሽ መልከ ሰዲ በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ሃይል ኮርፖሬሽን ሊገነባ የታቀደው የሃይል ማመንጫ ፕሮጀክት 137 ነጥብ 5 ሜጋ ዋት ሃይል የሚያመነጭ ነበር።

እንፋሎቱን ወደ ኤሌክትሪክ ሃይል ለመቀየር የተያዘውን ፕሮጀክት በበላይነት የሚመራው አሁን በወህኒ የሚገኙት ጄኔራል ክንፈ ዳኘው በሚመሩት ሜቴክ ሲሆን ለፋብሪካው ግንባታና የመሳሪያ ተከላ ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ሃይል ኮርፖሬሽን የ36 ሚሊየን ዶላር ክፍያ ተቀብሏል።

ለመሳሪያው ተከላ የሚያስፈልገው የመሬት ድልደላ ስራ ተሟልቷል በሚል የተርባይን ተከላ ከተጀመረ በኋላ መሬቱ ተርባይኑን መሸከም የማይችል መሆኑ ተረጋግጧል።

ባልተጠና መሬት ላይ የሃይል ማመንጫውን የግንባታ ስራ ከመስራቱ በተጨማሪ የሃይል ማመንጫውን መሳሪያ ለመትከል የሚያስፈልጉት ቁሳቁሶች አሮጌና እንዲሁም ያልተሟሉ ሆነው በመገኘታቸው ሜቴክ 36 ሚሊየን ዶላር ከተቀበለ በኋላ ስራው ሙሉ በሙሉ መቋረጡና ሒደቱም መክሸፉን ከቅርብ ምንጮች መረዳት ተችሏል።

መሳሪያዎቹን ፋብሪካው ላይ ለመግጠም ኮንትራት የወሰደው የቻይና ኩባንያ በሜቴክ የቀረቡት እቃዎች ያልተሟሉ እንዲሁም አሮጌዎች በመሆናቸው መግጠም አልችልም በማለቱ ሒደቱ ሙሉ በሙሉ መስተጓጎሉን ለማወቅ ተችሏል።

ሜቴክ አዲስ ናቸው በሚል ያስገባቸውና በአጠቃላይ 36 ሚሊየን የአሜሪካን ዶላር የወሰደባቸው ንብረቶች በተከማቹበት ቦታ እየተበላሹና ሳር እየበቀለባቸው መሆኑንም መረዳት ተችሏል።