በመተከል ለረጅም አመታት የቆዩ ህዝቦች ከአካባቢውን ለቀው እንዲሄዱ እየተደረገ ነው

ግንቦት ፲፬ (አስራ አራት) ቀን ፳፻፬ ዓ/ም

ኢሳት ዜና:-በመተከል ዞን -ዳንጉር ወረዳ ውስጥ ለእርሻ ሥራ ሄደው  ለረጅም አመታት የቆዩ የአማራና የአገው ብሔር ተወላጆች በክልሉ ካድሬዎች ለጅምላ እስራት ከመዳረጋቸውም በላይ ካለምንም ቅድመ ሁኔታ አካባቢውን ለቀው እንዲሄዱ እየተደረገ መሆኑን ፍኖተ-ነጻነት ዘገበ።

በተጠቀሰው አካባቢ  የአማራና የአገው ተወላጆች ለጅምላ እስራት መዳረጋቸውን ተከትሎ የወረዳው የሃይማኖት አባት ሰዎቹ የታሰሩበት እስር ቤት ድረስ በመሄድ፦ “ወዶ አማራና አገው ሆኖ የተፈጠረ ሰው የለም፤ እንዲሁም በፍላጐት ጉሙዝና ሽናሻ ሆኖ የተፈጠረ የለም፡፡ ሁላችንም የእግዚአብሔር የእጅ ስራዎች ነን፤ ስለዚህ የታሰሩ ዜጎች በአስቸኳይ ይፈቱ!” እያሉ እያለቀሱ ሲለምኑ፤ የወረዳው ሹሞች ለእኚህ አባት ልመና በፌዝ ምላሽ እንደሰጧቸው ምንጪቹ ተናግረዋል።

ከዚህም በላይ  በመተከል ዞን ፤” ኤዲዳ “ ቀበሌ ውስጥ ባላቸው የተገደለባቸው የመንታ ልጆች እናት  ጎረቤቶቻቸው ሢሰደዱ አቅማቸው በመድከሙ  አብረው መሄድ እንዳልቻሉ በመግለጽ፤  ለሚመለከታቸው አቤት ቢሉም፦ “አገርሽ ክልል 6 ሳይሆን ክልል 3 ነው፤ ስለዚህ ወደ አገርሽ ሂጂ” የሚል ምላሽ ተሰጥቷቸዋል።

እንደ ዜናው ምንጮች ዜጎች ለረዥም ዓመታት ይኖሩበት ከነበረው አነስተኛ ያዞታቸው እየተፈናቀሉ እንዲሰደዱ እየተደረገ ባለበት በዚሁ   በዳንጉር ወረዳ  ዙሪያ ፤በአሁኑ ጊዜ ለአንድ የውጪ ባለሀብት እስከ ሃያ ሺህ ሄክታር ድረስ እየተሰጠ ነው።

በሁኔታው ሀዘን የተሰማቸው የአካባቢው ተወላጆች፦ “ዜጎች በአገራቸው ሰርተው እንዳይበሉ መደረጉና  ኢህአዴግ ከዜጎች ይልቅ ለባዕዳን ትኩረት መስጠቱ፤ ኢትዮጵያዊነታችን ትልቅ አዘቅት ውስጥ መግባቱን ያመላክታል” ሲሉ ተናግረዋል።

አንደ ጋዜጣው ዘገባ፤ የግዳጅ ማፈናቀሉን ተግባር ተከትሎ ተፈናቃዮቹ  ገበሬዎች ከብቶቻቸውን እና የተለያዩ የቤት እንስሶቻቸውን እጅግ ርካሽ በሆነ ዋጋ ለመሸጥ ቢሞክሩም የሚገዛቸው ሊያገኙ አልቻሉም፡፡

በተያያዘ ዜና በማንዱራ ገነተማርያም ኤሲፃ ቀበሌ ገበሬ ማህበር ውስጥ  ከጉሙዝ ማህበረሰብ ጋር አብረው በፍቅር የሚኖሩ 86 አባወራዎች መካከል 82ቱ አባውራዎች ካለምንም ቅድመ ሁኔታ በአስቸኳይ ይዞታቸውንና አካባቢውን ለቀው እንዲወጡ መመሪያ መተላለፉን ለማወቅ ተችሏል፡፡

ኢሳት የአካባቢውን ነዋሪዎች ለማነጋገር ባደረገው ጥረት እየተፈናቀሉ ያሉት ዘጎች ከ1991 ዓም ጀምሮ የሰፈሩ ናቸው። ሰዎቹ በአካባቢው ለርጅም ዘመን የቆዩ እና ቤተሰብ መስርተው የኖሩ ናቸው። አንድ ስሙ እንዳይጠቀስ የፈለገ መሀንዲስ እንደገለጠው፣ ከክልሉ እንዲወጡ የተደረጉት ነዋሪዎች ከአማራ ክልል የመጡ እና ለረጅም ጊዜ በአካባቢው ሰፍረው የልማት ስራ ሲሰሩ የነበሩ ናቸው። ሰዎቹ በህገ ወጥ መንገድ ሰፍረዋል ከተባለ ህጋዊ ማድረግ አይቻልም ነበር ወይ የሚል ጥያቄ የቀረበለት መሀንዲሱ፣ በክልሉ ያልተነካ ሰፊ ድንግል መሬት ያለ መሆኑን አስታውሶ፣  እርምጃው ፖለቲካዊ ይዘት ያለው ሊሆን እንደሚችል ተናግሯል። ወደ ክልሉ የመጡ በተለይ የአንድ ብሄር ተወላጆች ሰፋፊ የእርሻ ስራ ይሰራሉ ተብሎ ቢጠበቅም፣ እስካሁን ድረስ እየሰሩ ያለው ደኖችን እየመነጠሩ ከሰል ማክሰል እና ወደ ሱዳንና መሀል አገር መላክ ነው ያለው መሀንዲሱ፣ በኢንቨስተር በተባሉ አጭበርባሪ የህወሀት ታጋዮች ላይ እርምጃ ከመውሰድ፣ ለዘመናት አካባቢውን እያለሙ የሚገኙትን ዜጎች ማፈናቀሉ ተቀባይነት የለውም ሲል አክሎአል።

አምና በፓዌ አካባቢ የነበሩ ከአማራ ክልል የመጡ ነዋሪዎች መባረራቸውን በማስታወስ ሰዎችን ማፈናቀል በዚህ አመት አለመጀመሩን የገለጠው መሀንዲሱ፣ ድርጊቱ ሊቀጥል የሚችል ነገር መሆኑንም ጠቁሟል።

ከደቡብ ክልል ጉራፈርዳ ወረዳ የአማራ ተወላጆች እየተመረጡ ሲፈናቀሉ የአካባቢው ነዋሪዎች መቃወማቸው ይታወቃል።

ስለተፈናቀሉት የአማራ ተወላጆች በፓርላማ ጥያቄ የቀረበላቸው አቶ መለስ ዜናዊ፤አብዛኛውን እውነታ በማድበስበስ እና በማስተባበል ከማለፋቸውም ባሻገር፤ የክልሉ መንግስት እርምጃ ደን በጨፈጨፉ ላይ እርምጃ እንደወሰደ መናገራቸው ይታወሳል።

የ አቶ መለስን ምላሽ ሰሙ ወገኖች፦ ኢትዮጵያው ውስጥ  በአንድ አካባቢ የሚኖር  አንድ ኢትዮጵያዊ  ደን ቢጨፈጭፍ  በአገሪቱ ህግ መሰረት ይጠየቃል እንጂ፤ ደን ስለጨፈጨፍክ በዚህ ክልል መኖር አትችልም ተብሎ እንዲሰደድ ይደረጋል?” ሲሉ ይጠይቃሉ።

በሌላ ዜና ደግሞ በሰሜን ጎንደር ዞን  በምዕራብ አርማጭሆ ወረዳ  አርሶ አደሮች በግዳጅ  እንዲፈናቀሉ በመደረጋቸው ምክንያት በመንግስት እና በአካባቢው ነዋሪዎች መካከል ውጥረት መንገሱን ጋዜጣው ዘግቧል

መንግስት የአካባቢውን አርሶ አደሮች መሬት በመንጠቅ፤ የተሸነሸኑ መሬቶች ላይ እንዲያርሱ ማድረጉ አርሶአደሮቹን ክፉኛ እንዳስቆጣ  የገለፁት የአካባቢው ነዋሪዎች፤ የተፈጠረው ውጥረት እና ፍጥጫ እየተካረረ በመምጣቱ መንግስት ትጥቅ የማስፈታት እንቅስቃሴ መጀመሩን ተናግረዋል።

መንግስት ፦”መሳሪያችሁን አስመዝግቡ”በሚል ሰበብ መሳሪያዎችን መንጠቅ እንደጀመረ እና እስካሁን የ 20 ሰዎችን መሳሪያ አስፈትቶ እንደወሰደም ነዋሪዎቹ  አመልክተዋል።

የአርሶ አደሮቹ መሬት የተወሰደውም፤ ለሱዳን ባለሀብቶች ለመስጠት እንደሆነ ነዋሪዎቹ ጨምረው ገልጸዋል።

በአሁኑ ሰዓት የአካባቢው አርሶ አደሮች ተቃውሞ እያየለ በመምጣቱ ግጭት ሊፈጠር ይችላል የሚል ስጋት ማየሉን የጠቆሙት ነዋሪዎቹ፤ በዚህም ሥጋት ሳቢያ  መንግስት ስልክን ጨምሮ  ወደ አካባቢው የሚደረጉ ማናቸውንም  ግንኙነቶች እንዲቋረጡ ማድረጎን አስታውቀዋል።

___________________________________________________________________________________________________________________________________________________

ESAT is the first independent Ethiopian satellite service tasked to produce accurate and balanced news and information, as well as other entertainment, sports and cultural programming created for and by Ethiopians.

ESAT is committed to the highest standards of broadcast journalism and programming and will strive to provide an outlet of expression to all segments of the diverse Ethiopian community worldwide