በመቀሌ ነገ ሰላማዊ ሰልፍ ሊደረግ ነው

(ኢሳት ዲሲ–ሕዳር 28/2011)በመቀሌ ነገ ቅዳሜ ለሁለተኛ ጊዜ ሰላማዊ ሰልፍ ሊደርግ መሆኑ ታወቀ።

እየተካሄደ ያለው የለውጥ ሂደትና በወንጀል በተጠረጠሩ ግለሰቦች ላይ እየተወሰደ ያለው ርምጃ የትግራይን ህዝብ ለማንበርከክ ነው በሚል ተቃውሞ ከአንድ ሳምንት በፊት በተለያዩ የትግራይ ክልል ከተሞች የተካሄዱት ሰልፎች ተከታይ የሆነው የነገው ሰልፍ ከፍተኛ ወጪ ተደርጎበት የሚካሄድ መሆኑ ታውቋል።

ፋይል

የትግራይ ክልል ኮሚኒኬሽን ቢሮ የመቀሌውን ሰልፍ በቀጥታ እንዲያሰራጩለት ለተለያዩ የቴቪዥን ድርጅቶች የትብብር ደብዳቤ መላኩም ታውቋል።

መቀሌ በዋዜማው የሱዳንና የኦነግን ጨምሮ በተለያዩ ሰንደቅ ዓላማዎችና አርማዎች መድመቋን የደረሰን መረጃ አመልክቷል።

መቀሌ ሽር ጉድ ላይ ናት። የአቶ መለስ ዜናዊና ዶክተር ደብረጺዮን ገብረሚካዔል ምስሎች ያሉባቸው ቲሸርቶችን በለበሱ ነዋሪዎች ደምቃለች።

ነገ ሰልፍ ተጠርቶባት ከዋዜማው ጀምሮ ዝግጅቷን እያደረገች ነው።

በከተማዋ ዋና ዋና አደባባዮች የተለያዩ ሀገራትና ድርጅቶች ሰንደቅ ዓላማዎች ተሰቅለዋል።

ከሃገራት የሱዳንና የኢትዮጵያ፣ ከድርጅቶች ደግሞ የህወሃትና የኦነግ አርማዎች ተተክለዋል።

ሰላማዊ ሰልፍ፣ የተቃውሞ ትዕይንት አይታ ለማታውቀው መቀሌ ባለፉት ወራት ተደጋጋሚ ሰልፎች እየደተረጉባት ነው።

በተቀረው የኢትዮጵያ ክፍል ለውጡን በመደገፍ ኢትዮጵያውያን ከዳር እስከዳር አደባባይ በወጡባቸው ቀናት መቀሌም ተቃራኒ ዓላማ ያነገቡ፣ ለውጡ ትግራይን ለማዳከም ያለመ በመሆኑ እንቃወማለን የሚል መልዕክቶች የተላለፉባቸው ሰልፎችን ስታስተናግድ ቆይታለች።

ባለፈው ሳምንትም ከአድዋ እስከሰቲት ሁመራ በ8 ከተሞች በተደረጉ ሰልፎች ህገመንግስቱ ይከበር፣ ራያና ወልቃይት የትግራይ አካል ናቸው፣ የመልካም አስተዳደር እንጂ የማንነት ጥያቄ የለንም፣በፌደራል መንግስቱ በኩል እየተወሰደ ያለው ርምጃ የትግራይን ህዝብ ለማጥቃት የተደረገ ርምጃ ነው የሚሉ መልዕክቶችና መፈክሮች ተላልፈው እንደነበረ የሚታወስ ነው።

ነገም መቀሌ ተመሳሳይ መልዕክቶች የሚተላለፉበትን በዓይነቱ የተለየ ትዕይነተ ህዝብ ልታካሂድ ተሰናድታለች።

ከዋዜማው ጀምሮ ዝግጅቱ የደመቀባት መቀሌ በነገው ዕለት በህወሃት ዓርማ ትጥለቀለቃለች ተብሎ ይጠበቃል።

ህገመንግስቱ ይከበር የሚለው መልዕክት የነገው ሰልፍ ዋና መሪ ሃሳብ እንዲሆን መታቀዱን ለማወቅ ተችሏል።

በከፍተኛ የሙስና ወንጀልና በሰው ልጅ ላይ በፈጸሙት ሰብዓዊ መብት ጥሰት ተጠርጥረው ለፍርድ የቀረቡ የደህንነትና የሜቴክ አመራሮች በማንነታቸው ምክንያት ነው የታሰሩት የሚለው ነገ ከመቀሌ የሚሰማው መልዕክት እንደሚሆን ለማወቅ ተችሏል።

ሰልፉን በቀጥታ ቴሌቪዥን እንዲያስተላልፉለት የትግራይ ክልል ኮሚኒኬሽን ቢሮ ለአማራ መገናኛ ብዙሃን  ድርጅት፣ ለአዲስ ቲቪ፣ ለኦሮሚያ ብሮድካስቲንግ ኔትወርክና ለኦሮሞ ሚዲያ ኔትወርክ በትብብር ደብዳቤ ጠይቋል።