በለገጣፎ የተጀመረው ቤትን የማፍረስ ዘመቻ ህግን መሰረት ያደረገ ነው ተባለ

(ኢሳት ዲሲ–የካቲት 14 /2011)በለገጣፎ የተጀመረው ቤትን የማፍረስ ዘመቻ  ህግን መሰረት ያደረገ መሆኑን የኦሮሚያ ክልል መሬት አስተዳደርና አጠቃቀም ቢሮ ሃላፊ ዶክተር ሚልኬሳ ሚደግሳ ተናገሩ።

በጉዳዩ ዙሪያ ጋዜጣዊ መግለጫ የሰጡት የቢሮ ሃላፊው በለገጣፎ እየተወሰደ ያለው እርምጃ የሊዝ አዋጅ 721ን መሰረት ያደረገ መሆኑን ቢሮ ሃላፊው ገልጸዋል።

የኦሮሚያ ክልል መሬት አስተዳደርና አጠቃቀም ቢሮ ሃላፊ ዶክተር ሚልኬሳ ሚደግሳ እንደገለጹት እርምጃው ከተሞች ስርዓት ባለውና ዓለም አቀፍ ደረጃውን በጠበቀ መልኩ እንዲያድጉ ለማድረግ ያለመ ነው።

በለገጣፎ  በወንዞች ዳርቻና አረንጓዴ ስፍራዎች ጉዳዩ ሕገ ወጥ መሆኑ እየታወቀ ግንባታዎች ተከናውነዋል ብለዋል።

ከዚህ ባለፈም ግንባታዎቹ ለመኖሪያ ምቹ ባልሆኑ ስፍራዎች የሚካሄዱ በመሆናቸው መንግስት ተጠያቂ የሚሆንበትን እድል ይፈጥራል ሲሉም ነው የገለጹት።

ዶክተር ሚሊኪያስ በመግለጫቸው 2004 ዓመተ ምህረት ላይ የወጣውን የሊዝ ህግ ለማስፈፀም 2005 ዓም  ላይ መመሪያ መውጣቱን አስታውሰዋል።

መመሪያውም ከ2005 ዓመተ ምህረት በፊት የተገነቡ ቤቶች ከሳይት ፕላኑ ጋር የሚጣጣሙ ከሆነ ህጋዊ እንዲሆኑ፤ ከፕላኑ ጋር የማይጣጣሙ ከሆነ ደግሞ እንደሚፈርሱ ያስቀምጣል ነው ያሉት።

እናም አሁን እየተወሰደ ያለው እርምጃም ከዚህ አንጻር መሆኑን ነው ያስረዱት።

በጥናቱም በአንዳንድ አካባቢዎች መንግስት ለአርሶ አደሩ ካሳ ከፍሎ ለልማት ባዘጋጃቸው ቦታዎች ላይ ህገ ወጥ ግንባታ መካሄዱንም ጠቅሰዋል።

በቀበሌ ቤቶች ሳይቀር ግለሰቦች የፈለጉትን ዓይነት ግንባታ አከናውነው መገኘታቸውም በጥናቱ ተደርሷል።

ግንባታው ህገ ወጥ መሆኑ እየታወቀ ግንባታ መካሄዱም ትልቁ ችግር መሆኑን ጠቅሰው፥ መንግስትም ህግ የማስከበር ስራ እያከናወነ ነው ብለዋል።

በቅርቡ በአዳማ፣ በሻሸመኔ እና መቱ ከተሞች በሺዎች የሚቆጠሩ ህገወጥ ግንባታዎች መፍረሳቸውን በማንሳትም፥ እርምጃው በፍንፊኔ ዙሪያ ብቻ እየተወሰደ አለመሆኑን ገልፀዋል።

ዶክተር ሚልኬሳ እርምጃ በተወሰደባቸው አካባቢዎች ነዋሪዎቹ ቤታቸውን እንዲያፈርሱ ከአንድ አመት ጀምሮ ማስጠንቀቂያ ሲሰጣቸው እንደቆየም አስታውሰዋል።