በለውጥ ስም ሃገርን የሚበታትን ተግባር ሊቆም ይገባል ተባለ

(ኢሳት ዲሲ–የካቲት 18/2011)የሕወሐት ማዕከላዊ ኮሚቴ በለውጥ ስም ሀገርን የሚበታትን ተግባር ሊቆም ይገባል ሲል ማስጠንቀቂያ ሰጠ።

የህወሓት 44ኛው የምስረታ በአልን ምክንያት በማድረግ የማዕከላዊ ኮሚቴው ባወጣው መግለጫ የሀገሪቱን ህገመንግስትና ፌደራላዊ ስርዓቱን ለማፍረስ የውስጥ ትምክህት ሀይልና ጸረ ልማት የሆኑ የውጭ ሀይሎች አንድ ላይ በመቀናጀት ከፍተኛ ርብርብ እያደረጉ ይገኛሉ ብሏል፡፡

እናም የትግራይ ሕዝብና ብሄር ብሄረሰቦች እንዲሁም የአብዮታዊ ዲሞክራሲ ህይሎችና አጋር ድርጅቶች በትምክህትና በጥገኝነት ላይ የምታደርጉትን ትግል አጠናክራችሁ እንድትቀጥሉ ህወሓት ጥሪውን ያቀርባል ብሏል ማዕከላዊ ኮሚቴው፡፡

የትግራይ ህዝብ ትጥቅ ትግል የጀመረበትና የህወሓት 44ኛው የምስረታ በአል ብትግራይና በአካባቢው ነባር መስራቾቹና አባላቱ በተገኙብት ተከብሯል።

በዚሁ በመቀሌ በተከበረው የየካቲት 11 በዓል በሕወሐት ክፍፍል ጊዜ ከድርጅቱ የተባረሩት አቶ ስየ አብርሀና ጄናራል ጻድቃን ገብረ ትንሳኤን ጨምሮ ሊሎችም ነባር ታጋዮች ተገኝተዋል።

ሕወሐት በመግለጫው ታዲያ ይሕ 44ኛ የምስረታ በዓል የሚከበረው ኢትዮጵያ የጀመረችውና መላው አለም የመሰከረለት የእድገት ጉዞ ወደ ኋላ በተቀለበስበት ፣ የብልፅግና ጉዞ ወደ ስጋትና ጭንቀት እየተቀየረ ባለበት ወቅት ነው ብሏል ።

በአሁኑ ጊዜ በኢትዮጵያ ሰላምና መረጋጋት እየጠፋ የሄደበት፣ የመላ ህዝቦች መሰረታዊ ፍላጎቶች የሆኑት ልማትና ዴሞክራሲ ወደ ጎን ተብለው፣ የተጀመረው ፈጣን፣ ተከታታይና ፍትሀዊ የልማት እድገት ችግር ውስጥ የወደቀበት፣ ከድህነት በፍጥነት መውጣት የተጀመረበት ሁኔታ ተቀልብሶ የቁልቁለት መንገድ እየተጀመረ የመጣበት ሁኔታ እየታየ ሲልም ሕወሐት በመግለጫው አትቷል።

ሀገራችን ባለፉት 27 አመታት ሰላሟ ተጠብቆ፣ ክብሯንና ልኣላውነቷን አስከብራ፣ በአጭር ጊዜ ውስጥ የፈጣንና ፈርጀ ብዙ ማህበረ-ኢኮኖሚ እድገት ተምሳሌት መሆን የጀመረች፣ ከራስዋ አልፋ የጎረቤት ሀገሮች አለኝታ ወደ መሆን ተሸጋግራ እንደነበረችም ይታወሳል ብሏል ሕወሐት።

ዛሬ  ግን ለራስዋ መሆን አቅቷት፣ ዜጎች በሰላም ወጥተው በሰላም ለመመለስ የሚቸገሩባት፣ በሀገሪቱ ታሪክ ታይቶ በማይታወቅ ደረጃ የዜጎች መፈናቀልና ግጭት የዘወትር ተግባር የሆነባት፣ ዜጎች በማንነታቸው ብቻ ለተለያየ ጥቃቶች የሚጋለጡባት፣ ከምንም ጊዜ በላይ የዜጎች ህይወትና ንበረት ዋስትና ያጣበት ሁኔታ እየተከሰተ የመጣበት፣ የሀገሪቱና የህዝቦቿ መሰረት የሆነው ሕገ መንግስትና ፌዴራላዊ ስርአት በጠራራ ፀሀይ እየተናደና አደጋ ላይ ወድቋል ሲልም ለወጡኝ አጣጥሎታል።

በስመ ለውጥ ለሀገራቸው ክብርና ሉኣላዊነት መረጋገጥ ዕደሜ ልካቸውን የደከሙና የለፉ የሚረገሙበትና የሚብጠለጠሉበት፣ በሀገሪቱ ታሪክ ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ በዜጎች ላይ የተለያዩ በደሎችና ግፍ የፈፀሙ እንዲሁም የሀጋራችን ሉኣላዊነት አሳልፈው የሰጡ ብቻ ሳይሆን ከሌሎች የኢትዮዽያ ጠላቶች ጋር አብረው ሀገርና ህዝብ የወጉ የሚመሰገኑበትና ክብር የሚሰጥበት የክህደት ዘመን ደርሰናልም ነው ያለው።

እንደ ሕወሃት ማዕከላዊ ኮሚቴ መግለጫ  ሕገ መንግስቱና ፌዴራላዊ ስርአቱ አደጋ ላይ እየወደቀ ነው፣ ብሄር መሰረት ያደረገ ጥቃትና መፈናቀል ይቁም ብሎ የሚታገል ወገን ለተለያዩ ጥቃቶችና በደሎች ተጋልጧል።

ሕገ መንግስቱ እንዲጣስ ከፍተኛ ሚና የተጫወቱ፣ፌዴራላዊ ስርአቱ በጠራራ ፀሓይ የጣሱ፣ ሰላማዊ ዜጎች ያፈናቀሉና ማንነት ላይ የተመሰረተ ጥቃትና ግድያ ለፈፀሙ አካላት ግን በገሀድ እውቅናና ሽልማት ይሰታል ብሏል ።

የዚህ ሁሉ ችግር መሰረታዊ ምክንያትም ሕወሃት እንደሚለው በኢህአዴግ አመራር ውስጥ እየተንከባለሉ የመጡ የጥገኝነት አስተሳሰብና ተግባር /አደጋ/ ወደ ከፋ ደረጃ በመድረሱ መሆኑ ሊሰመርበት ይገባል።

ከዚህ ቀደም በኢህአዴግ አመራር የተጀመረውን በጥልቀት የመታደስ ሂደት በጋራ በተቀመጠው አቅጣጫ ባለመሄዱና በመከለሸቱ እንዲሁም የውጭ ሀይሎች ጣልቃ ገብነት በመኖሩ ጭምር ነውም ብሏል።

በህዝቦች መራራ ትግልና በተከፈለው ክቡር መስዋእትነት የተገነባችው አዲስቷ ኢትዮጵያ ያልተዋጠላቸው ሃይሎች፣ የህዝቦች አንድነት መሰረት የሆነውን ስርአት ለመናድ ሌት ተቀን እየተንቀሳቀሱ ይገኛሉ።

በተለያየ የአለም ክፍሎች ተበታትኖ የነበረው የትምክህት ሀይሎች ግንባር ፈጥረው፣ ባለ በሌላ ጉልበቱ በትግራይ ህዝብና መሪው ድርጅት ህወሓት ላይ በከፍተኛ ደረጃ ሲዘምቱ እያየን ነው።

የሁሉም ጥፋት ተጠያቂ ወያኔ፣ በሁሉም አካባቢ ለሚፈጠረው ማንኛውም ጉዳይም ጭምር ተጠያቂው ወያኔ ነው እያሉ፣ ከወንድሙ የኢትዮጵያ ህዝብ ሊነጥሉት በላቀ አኳኋን እየተንቀሳቀሱ ነውም ብሏል የሕወሐት መግለጫ።

የሕወሐት ማዕከላዊ መግለጫ እንዳለው  ሕገ መንግስቱንና ፌዴራላዊ ስርአቱን ለመናድ የሚደረገውን ሽለላና ተንኮል ፍፁም ተቀባይነት የለዉም።

እናም የትግራይ ህዝብና ህወሓት በዚህ ጉዳይ ፍፁም እንደማይደራደሩ ሁሉም ሊገነዘበው ይገባል አው ያለው።

የትግራይ ህዝብ በከበባ ውስጥ በማስገባት አሜን ብሎ የሚምበረክ ወይም አንገቱ ደፍቶ ሊኖር ይችላል ብሎ የሚገምት አካል ካለ፣ አንድም የትግራይን ህዝብ የማያውቅ፥ አልያም ታሪኩን የማይረዳ ነዉም ብሏል ።

አሁንም ትክክለኛ የትግል ስልትና ስትራቴጂ ይዘን፣ ለማንኛው ሀይል ተንበርክኮና እጅ ሰጥቶ የማያውቅ ህዝባችን ይዘን የማንሻገረው ወንዝና የማንወጣው ዳገት/አቀበት/ የለም፤ አይኖርምም ነው ያለው  ሕወሃት በመግለጫው።

በመሆኑም የትግራይ ሕዝብና ብሄር ብሄረሰቦች እንዲሁም የአብዮታዊ ዲሞክራሲ ህይሎችና አጋር ድርጅቶች በትምክህትና በጥገኝነት ላይ የምታደርጉትን ትግል አጠናክራችሁ እንድትቀጥሉ ህወሓት ጥሪውን ያቀርባል ብሏል ማዕከላዊ ኮሚቴው፡፡