በሃይለ ገብረስላሴና በእንግሊዛዊው አትሌት ሞህ ፋራህ መካከል የተፈጠረው ውዝግብ ተካረረ

(ኢሳት ዲሲ–ሚያዚያ 18/2011) በኢትዮጵያዊው ሃይለ ገብረስላሴና በእንግሊዛዊው አትሌት ሞህ ፋራህ መካከል የተፈጠረው ውዝግብ መካረሩ ተገለጸ።

በአትሌት ሃይሌ ሆቴል በነበረኝ ቆይታ ዘረፋ ተፈጽሞብኛል ላለው ሞህ ፋራህ ሃይሌ መልስ መስጠቱ ውዝግቡን እንዳከረረው ዴይሊ ቴሌግራፍ ዘግቧል።

ፋይል

አትሌት ሃይሌ እንደሚለው ሞህ ፋራህ በሆቴል ቆይታው በሰዎች ላይ ድብደባ ፈጽሟል።

በስነምግባር ጉድለት ችግር ፈጥሮብኛል ሲል ሞህ ፋራን ከሷል።

የሁለቱ የዓለማችን ታላላቅ አትሌቶች ውዝግብ አለምዓቀፍ ትኩረት መሳቡን ለማወቅ ተችሏል።

ባለፈው ወር መጋቢት መጨረሻ ላይ ነው። የዓለም የረጅም ርቀት ሯጭና የተለያዩ ክብረወሰኖች ባለቤት እንግሊዛዊው ሞህ ፋራህ ኢትዮጵያ ነበር።

ሱሉልታ በሚገኘውና የአትሌት ሃይሌ ገብረስላሴ ንብረት በሆነው ያያ አፍሪካ አትሌቲክስ መንደር ነበር ያረፈው ሞህ ፋራህ።

መጋቢት 25 ጠዋት ሞ ፋራህ መዘረፉን በመግለጽ ለሆቴሉ አመራሮች ያሳውቃል።

ፋራህ እንደሚለው የሞባይል ስልኩ፣ የእጅ ሰዓቱና 2600 የእንግሊዝ ፓውንድ ገንዘቡ መሰረቁን ይገልጻል።

ሞህ ፋራህ እንደሚለው ሃይሌ መዘረፌን አሳውቄው ምንም ምላሽ አልሰጠኝም።

የለንደኑን የማራቶን ውድድር እንዲስተጓጎልብኝ ሆን ብሎ ያስደረገው ነው ሲል ሞህ ፋራህ አትሌት ሃይሌ ላይ ጠንካራ ክስ ያቀርባል።

ሃይሌ ከትላንት በስቲያ ዴይሊ ቴሌግራፍ ለተሰኘ የእንግሊዝ ጋዜጣ በሰጠው ፣ምላሽ የሞህ ፋራህን ክስ ከበቀል ስሜት የመነጨ ሲል አስተባብሎታል።

ለሶስት ሳምንታት በፖሊስ በተደረገ ምርመራ ምንም ዓይነት የተሰረቀ ንብረት እንደሌለ ተረጋግጧል ያለው አትሌት ሃይሌ ገብረስላሴ ጉዳዩ  በክብሬ ላይ የተቃጣ የበቀል ርምጃ ነው ብሏል።

እንደውም ሞህ ፋራህ በሆቴሉ በነበረው ቆይታ በስፖርት ማበልጸጊያ ክፍል ውስጥ በአንድ አትሌት ላይ ድብደባ መፈጸሙንና የሆቴሉን ጸጥታ ማወኩን በመግለጽ ተገቢ ባህሪ የሌለው ሲል ወርፎታል።

የያያ አፍሪካ አትሌቲክስ መንደር ስራ አስኪያጅ አቶ ለሚሳ ቦቴ ለዴይሊ ቴሌግራፍ በሰጡት ምላሽ ሞህ ፋራህ በሆቴሉ በነበረው ቆይታ ሰራተኞችን በመዝለፍና በማዋረድ አስነዋሪ ተግባር ሲፈጽም ነበር።

ለተጠቀመበት የሚፈለግበትን የ2000 ፓውንድ ክፍያ ሳይፈጽም ሄዷልም ሲሉ አቶ ለሚሳ ገልጸዋል።

ሞህ ፋራህ በአትሌት ሃይሌ ምላሽ መበሳጨቱን የገለጸ ሲሆን ጉዳዩን በቀላሉ እንደማይመለከተው አስታውቋል።

የሁለቱ የአለማችን ታላላቅ አትሌቶች የከረረ ፍጥጫ ከቃላት መወራወር ባለፈ ወዴት ሊያመራ እንደሚችል የታወቀ ነገር የለም።