ሼህ መሐመድ አላሙዲ ከእስር ተፈቱ

(ኢሳት ዲሲ–ጥር 20/2011)ሼህ መሃመድ ሁሴን አሊ አላሙዲ ከእስር  መፈታታቸውን የቅርብ ምንጮቻቸው አረጋገጡ።

ትውልደ ኢትዮጵያዊው ቢሊየነር ሼህ መሃመድ ሁሴን አሊ አላሙዲ ከእስር ተፈተዋል ቢባልም የተፈቱበት ሁኔታ ባለመታወቁ ከሳወዲ አረቢያ የመውጣት መብት ይኑራቸው እይኑራቸው የተረጋገጠ ነገር የለም።

ሼህ መሀመድ ከእስር ስለመፈታታቸው ግን የሚድሮክ ጺትዮጵያ ዋና ስራአፈጻሚ ዶር አረጋ ለኢሳት አረጋግጠዋል።

ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ሼክ መሃመድ መፈታታቸውን ከህግ አማካሪያቸው ተካ አስፋው አረጋግጧል፡፡

ሼክ መሃመድ በአሁኑ ወቅት በእስር ከቆዩበት ሪያድ በመነሳት ጅዳ ወደሚገኘው መኖሪያ ቤታቸው በመጓዝ ላይ ይገኛሉ፡፡

ሼክ መሃመድን ከእስር ለማስፈታት የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐብይ አህመድ ተደጋጋሚ ጥረት ሲያደርጉ መቆየታቸው የሚታወስ ነው፡፡

ከእስር መፈታታቸውን ተከትሎም ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሰላም እንዲመለሱ መልካም ምኞት መግለጻቸውን ከጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ወደ ሳዑዲ አረቢያ በተጓዙበት ወቅት ከአልጋ ወራሽ ቢን ሳልማን ጋር ከተወያዩባቸው ጉዳዬች መካከል የመሀመድ አል አሙዲ መለቀቅ አንዱ ነበር።