ሼህ መሀመድ አላሙዲንን ጨምሮ ሌሎች የሳውዲ ባለሃብቶችና ልኡላን በዚህ ወር መጨረሻ ሊፈቱ ይችላሉ ተባለ

(ኢሳት ዜና–ሕዳር 20/2010)ትውልደ ኢትዮጵያዊው ሼህ መሀመድ አላሙዲንን ጨምሮ በቁጥጥር ስር የዋሉት የሳውዲ ባለሃብቶችና የልኡላን ቤተሰቦች በዚህ ወር መጨረሻ ሊፈቱ እንደሚችሉ አንድ የሳውዲ ባለስልጣን ገለጹ።

ከታሰሩት ውስጥ 95 በመቶው በድርድር ለመውጣት ፈቃደኛ መሆናቸውንም ቢቢሲ በዘገባው አስፍሯል።

በድርድሩ መሰረትም የተወሰነውን የሃብታቸውን መጠን ወደ ሳውዲ መንግስት ግምጃ ቤት ማስገባት እንደሚጠበቅባቸውም ተመልክቷል።

እጅግ ውድና ዘመናዊ በሆነው ሪትዝ ካርልተን ሆቴል ውስጥ የታሰሩት ባለሃብቶች በቁጥር 201 ያህል ሲሆኑ ሰራተኞችን ጨምሮ በአጠቃላይ 500 ያህል መሆናቸውንም ቢቢሲ ዘግቧል።

ከታሰሩት ውስጥ 7ቱ ቀደም ሲል የተለቀቁ ሲሆን ትላንት ማክሰኞ ደግሞ የቀድሞው ንጉስ አብዱላህ ልጅ ሚተብ ቢን አብዱላህ ከቢሊየን ዶላር በላይ ለመክፈል በመስማማት ሲፈቱ ሌሎች ተጨማሪ ሶስት ታሳሪዎች በድርድር ላይ መሆናቸው ተመልክቷል።

የ65 አመቱ ልዑል ሚተብ ቢን አብዱላህ የሳውዲ ብሔራዊ የክብር አዣዥ ሲሆኑ ወደ ወህኒ የተጋዙት በአጎታቸው ልጅ የ32 አመቱ አልጋወራሽ ልዑል መሀመድ ሰልማን ነው።

ትውልደ ኢትዮጵያዊውን ሼህ መሀመድ አላሙዲንን ጨምሮ በአጠቃላይ ከታሰሩት ሰዎች ጋር በተያያዘ 1 ሺ 9 መቶ የባንክ ሂሳቦች ታግደዋል።

የዚህ መጠን 800 ቢሊየን ዶላር ያህል መሆኑም ተመልክቷል።

ልዑላኑና ባለሃብቶቹ የታሰሩበትን ሪትዝ ካርልተን ሆቴልን እንድትጎበኝ የተፈቀደላትና ሆኖም ታሳሪዎቹን ፎቶ እንዳታነሳ የተከለከለችው የቢቢሲ ጋዜጠኛ ሊስ ዱሴት የጸረ ሙስና ኮሚቴውን አባል ጠይቃ እንደዘገበችው የሳውዲ አረቢያ መንግስት መቶ ቢሊየን ዶላር ያህል ከታሳሪዎቹ ለማስመለስ ወይንም ለመቀበል ይፈልጋል።

እስረኞቹ የእጅ ስልካቸውን ቢነጠቁም በሆቴል ክፍሎቹ በተዘረጋው ስልክ ከቤተሰብ ጋር መገናኘትም ሆነ ስራቸውን ማስኬድ እንዲችሉ ኢሜላቸውን ጭምር እንዲጠቀሙ ተፈቅዶላቸዋል።

እስረኞቹ የግል ጸጉር አስተካካይ እንዲሁም ልዩ ምግቦችና የግል ወጌሻዎችን ጨምሮ በርካታ ጥያቄዎችን እያቀረቡ ቢሆንም ተቀባይነት እንዳላገኙም ከቢቢሲ ዘገባ መረዳት ተችሏል።

ሙሉ ወጪው በሳውዲ አረቢያ መንግስት በተሸፈነው የሪትዝ ከርልተን ሆቴል ውስጥ ከታሰሩት እስረኞች ውስጥ 95 በመቶው በድርድር ማለትም ገንዘብ በመክፈል ወይንም በመመለስ ለመውጣት ፈቃደኛ ሆነዋል።

ከዚህም ጋር ተያይዞ በቅርቡ እንደሚፈቱ ተመልክቷል።

ታሳሪዎቹ በተያዘው የፈረንጆቹ አመት መጨረሻ ወይንም አዲሱ አመት መጀመሪያ ላይ ይፈታሉ ተብሎ ይጠበቃል።

በኢትዮጵያ በከፍተኛ ኢንቨስትመንት ውስጥ እየተሳተፉ የሚገኙት ሼህ መሀመድ አላሙዲን የተያዘባቸው የባንክ ሂሳብ እንዲሁም በድርድር ከፍለው የሚወጡት ገንዘብ በኢንቨትመንታቸው ላይ ስለሚያመጣው ተጽእኖ የታወቀ ነገር የለም።