ሳዑዲ አረቢያ ለኢትዮጵያውያን እስረኞች ምህረት አደረገች

(ኢሳት ዲሲ–ሚያዚያ 30/2011)በመጨረሻ ሳዑዲ አረቢያ የረመዳን ጾም መግባትን ምክንያት በማድረግ ለኢትዮጵያውያን እስረኞች ምህረት ማድረጓ ተገለጸ።

ፋይል

የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት እንዳስታወቀው 1 ሺህ 400 ኢትዮጵያውያን እስረኞች በሳዑዲ አረቢያ የረመዳን ምህረት ተጠቃሚ በመሆን ከእስር ተለቀዋል።

ኢትዮጵያውያኑ እስረኞች በተለያዩ ወንጀሎች የብዙ ዓመታት ቅጣት ተጥሎባቸው በሳዑዲ አረቢያ በተለያዩ ከተሞች በሚገኙ እስር ቤቶች ውስጥ የነበሩ መሆናቸው ታውቋል።

ከኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ እንደሚያመለክተው ሳዑዲ አረቢያ በእስር ላይ የሚገኙ ኢትዮጵያውያንን በምህረት ለመልቀቅ ውሳኔ ላይ የደረሰች ሲሆን በሮመዳን ጾም ምክንያት የተለቀቁት በተለየ የምህረት ውሳኔ ነው።

አሁን ከተለቀቁት በተጨማሪም አሁን በእስር ላይ የሚገኙ እስረኞች የፍርድ ጊዜያቸው በሶስት እጥፍ እንዲቀነስላቸው እንደሚደረግ የሳዑዲ አረቢያ ባለስልጣናት ቃል መግባታቸውንም  የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታውቋል።

በምህረት ከተፈቱት መካከል 300 የሚሆኑት ዛሬ ሌሊት ወደ ሀገራቸው  እንደሚመለሱም ተመልክቷል።