ሰላም ወዳድ ዜጋ ሁሉ ጦርነት ሊነሳ ይችላል ብሎ ስጋት ሊገባዉ አይገባም

 (ኢሳት ዲሲ–የካቲት 27/2011)የትግራይ ሕዝብና መንግስት ጦርነታቸዉ ከድህነት ጋር በመሆኑ ማንኛውም ሰላም ወዳድ ዜጋ ሁሉ ጦርነት ሊነሳ ይችላል ብሎ ስጋት ሊገባዉ አይገባም ሲል ይክልሉ ኮሚኒኬሽን ጽህፈት ቤት ገለጸ።

የአማራ ክልል ምክር ቤት ከትግራይ በኩል በመቀሌ የመሸገ ቡድን ትንኮሳ እየተፈጸመብኝ ነው በሚል  የተለያዩ ውሳኔዎች ማስተላለፉን አስመልክቶ  የክልሉ የመንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት መግለጫ አውጥቷል፡፡

የአማራ ክልል ምክር ቤት አስተላለፉዋቸው ከተባሉት ጉዳዮች መካከል የትግራይ ህዝብና መንግስት ጦርነት ለማካሄድ እያደረጉት ካለው ቅስቀሳና ዝግጅት እንዲቆጠቡ የሚል ማስጠንቀቅያ አዘል መልእክት አሰራጭቷል ሲል የትግራይ ክልል የመንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ፅ/ቤት ገልጿል ፡፡

የትግራይ ህዝብና መንግስት የጦርነት አስከፊነት ስለሚረዱ፣ ዋነኛ አጀንዳቸው የሆነው ሰላም ማስፈን፣ ዲሞክራሲ ማስፋትና መልካም አስተዳደር ማንገስ ነው ብሏል መግለጫው።

እናም የትግራይ ህዝብና መንግስት የታገሉለትን ህዝባዊ መሰመር አንግበዉ ወደፊት ከመገስገስ ዉጭ በወንድም የአማራ ህዝብ ላይ አፈሙዝ የሚያዞርበት አንዳች ምክንያት የላቸዉም ነው ያለው፡፡

ይልቅኑም ማነው በግላጭ ትንኮሳና የጦርነት አታሞ ሲጎስም የከረመው የሚል ጥያቄ ቢነሳ፣ ምላሹ ሰላም ወዳድ ዜጋ ምስክርነት ሊሰጥ ይችላል፡ ሲልም የአማራ ክልል ምክርቤትን ከሷል።

ሽፍቶች ጨምሮ የተለያዩ ፀረ-ሰላምና ፀረ-ልማት ሃይሎች የተለያዩ የሚድያ አማራጮችን ተጠቅመው፣ ላለፉት ሶስት ዓመታት፣ ያለእረፍት ቀንና ለሊት የጦርነት ቅስቀሳና ቱንኮሳ ከማካሄድ አልፈው የትግራይ ወሰኖችን  መለሱ ሲሉ ቆይተዋልም ብሏል ፡፡

ትላንት የትግራይ ክልል ብሄር ተወላጆች ብቻ በመሆናቸው በአማራ ክልል የተለያዩ ቦታዎች በድንጋይ ተቀጥቅጠው ሲገደሉ፣ ከ50 ሺ በላይ ዜጎች ጥረው ግረው ያፈሩት ሃብትና ንብረታቸዉ ተዘርፈው ሲፈናቀሉ፣ እንዲሁም የአማራና የትግራይ ህዝብ እንዳይገናኙ አውራ መንገዶችን ዘግቶ  የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት እንዲሻክር የተፍጨረጨረዉ ማነው ሲልም በደልና ክህደት እንደተፈጸመበት ገልጿል፡፡

በአጠቃላይ የትግራይ ህዝብና መንግስት ነጋ ጠባ ከፅንፈኛ ሃይሎች የሚወረወርባቸዉ የቃላት ጦርነትና ትንኮሳ ከልክ በላይ ያለፈ ቢሆንም፣ ጦርነት ለየትኛውም ወገን እንደማይጠቅም አሳምረዉ ስለምያዉቁ፣ እስከ አሁን ድረስ ትዕግስትን መርጠዋል ሲልም መግለጫው አመልክቷል፡፡

ስለሆነም ትላንትም ሆነ ዛሬ የትግራይ ህዝብና መንግስት ዋነኛ ጠላት ድህነት ነው፡፡ አሁንም ቢሆን ጦርነታቸዉ ከድህነት ጋር በመሆኑ ማንኛውም ሰላም ወዳድ ዜጋ ስጋት ሊገባዉ አይገባም ብሏል፡፡