ራይላ ኦዲንጋ በድጋሚ ከሚካሄደው ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ራሳቸውን በማግለላቸው በኬንያ ናይሮቢና በሌሎች ከተሞች ተቃውሞ ተቀሰቀሰ

(ኢሳት ዜና–ጥቅምት 1/2010) የኬንያ ፕሬዝዳንታዊ ዕጩ የነበሩትና ለሁለተኛ ዙር ከፕሬዝዳትን ኬንያታ ጋር ለመወዳደር ቀጠሮ የተያዘላቸው ራይላ ኦዲንጋ ከሒደቱ ራሳቸውን በማግለላቸው በኬንያ ናይሮቢና በሌሎች ከተሞች ተቃውሞ ተቀሰቀሰ።

ይህ በእንዲህ እንዳለ በላይቤሪያ በተካሄደውና የቀድሞው ታዋቂ የእግር ኳስ ተጫዋች ጆርጅ ዊሃ የተሳተፈበት ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ በሰላም ተጠናቆ ውጤቱ በመጠበቅ ላይ ነው።

እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር ነሀሴ 8/2017 በኬንያ በተካሄደው ምርጫ በውጤቱ ሁለተኛ ሆነው ያጠናቀቁት የተቃዋሚ ፓርቲው ዕጩ ራይላ ኦዲንጋ በምርጫ ስርአቱ ላይ ባነሱት ተቃውሞ የኬንያ ጠቅላይ ፍርድ ቤትም ጥያቄያቸውን በመቀበሉ ምርጫው በድጋሚ እንዲካሄድ መወሰኑ ይታወሳል።

በዚህም ከመራጮች ውስጥ ከግማሽ በላይ 54 በመቶ ድምጽ ያገኙት ፕሬዝዳንት ኡሁሩ ኬንያታና 44 በመቶ ድምጽ ያገኙት የተቃዋሚ ፓርቲው ዕጩ ራይላ ኦዲንጋ እንደገና እንዲወዳደሩ እንደአውሮፓውያኑ አቆጣጠር ለጥቅምት 26/2017 ቀጠሮ ተይዞ ነበር።

ሆኖም ዳግመኛ ምርጫው ሊካሄድ 15 ቀናት ያህል ሲቀረው ሚስተር ራይላ ኦዲንጋ ራሳቸውን ከምርጫው ማግለላቸውን ይፋ አድርገዋል።

የምርጫ ኮሚሽኑ የተጠየቀውን መሰረታዊ ለውጥ ባለማምጣቱ የቀደመውን ስህተት ከመድገም ውጭ መፍትሄ አይኖርም በማለት ራሳቸውን ለማግለል መወሰናቸውን ተናግረዋል።

እዚህ ውሳኔ ላይ የደረሱት ለኬንያ ሕዝብ ጥቅም እንዲሁም ለአካባቢውና ለአለም ሰላም ነው በማለት ራይላ ኦዲንጋ መግለጫ ቢሰጡም የራሳቸው ደጋፊዎች ምርጫ ኮሚሽኑን በማውገዝ በናይሮቢና በሌሎች ከተሞች አደባባይ በመውጣት ተቃውሞ አቅርበዋል።–በዚህም ከፖሊስ ጋር ተጋጭተዋል።

ምርጫው ይካሄዳል ወይንስ የፕሬዝዳንት ኡሁሩ ኬንያታ የቀድሞው ውጤት ይጸድቃል የሚለው ጉዳይ አነጋጋሪ ሆኗል።

የፕሬዝዳንቱ ደጋፊዎች ደግሞ የምርጫ ኮሚሽኑ ውጤቱን ይፋ እንዲያደርግና የኡሁሩ ኬንያታን አሸናፊነት እንደገና እንዲያውጅ በመጠየቅ ላይ ናቸው።

ይህ ዘገባ እስከተጠናቀረበት ጊዜ ድረስ ተቃውሞው እንደቀጠለ ነው።

ይህ በእንዲህ እንዳለ እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር ከ2006 ጀምሮ በሁለት ዙር ምርጫ የላይቤሪያ መሪ ሆነው በማገልገል ላይ የሚገኙት የሰላም ኖቬል ሽልማት አሸናፊ ኤለን ጆንሰን ሰርሊፍን ለመተካት የተካሄደው ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ በሰላም መጠናቀቁ ታውቋል።

በእርስ በርስ ጦርነት ስትታመስ የቆየችውና የቀድሞ መሪዋ ቻርለስ ቴይለር በአለም አቀፍ የጦር ወንጀለኞች ፍርድ ቤት የ50 አመታት እስራት ተፈርዶባቸው በብሪታኒያ ወህኒ ቤት በሚገኙበት ሰላሟን እያረጋገጠች ያለችው ላይቤሪያ 20 ያህል እጩዎች በተሳተፉበት ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ የቀድሞው ዝነኛው የእግር ኳስ ተጫዋች ጆርጅ ዊሃና ምክትል ፕሬዝዳንቱ ጆሴፍ ቦካይ በጊዜያዊው ውጤት በቅርብ ርቀት ተፎካካሪ መሆናቸው ተመልክቷል።