ማዕከላዊ የወንጀል ምርመራ ክፍል መዘጋቱ ተረጋገጠ

(ኢሳት ዲሲ–ታህሳስ 4/2011) ማዕከላዊ በመባል የሚጠራው የወንጀል ምርመራ ክፍል መዘጋቱን አረጋግጬአለሁ ሲል የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የህግ፣ ፍትህና ዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ገለጸ።

ኮሚቴው ማዕከላዊን ተዘዋውሮ ከጎበኘበኋላ በሰጠው መግለጫ ማዕከላዊ ተዘግቶ ክፍሎቹ ለቡራዩ ተፈናቃዮች በጊዜያዊ መኖሪያነት እያገለገሉ ነው ብሏል።

 የኮሚቴው አባላት አረጋገጥን እንዳሉትም በማዕከላዊ አንድም እስረኛ የለም።

የነበሩት 139 እስረኞችም ወደ አዲስ አበባ ፖሊስ ማረሚያ ቤት በአደራ መሰጠታቸውን ተረድተናል ብለዋል የኮሚቴው አባላት።

አባላቱ በሙስናና በከፍተኛ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ወንጀል ተጠርጥረው በህግ ቁጥጥር ስር የሚገኙትን የሜቴክና የደህንነት ባለስልጣናትንም ጎብኝተዋል።

የስንቱ ህይወት በጠዋቱ ተቀጥፏል። የአያሌ ኢትዮጵያውያን ወጣቶች ተስፋ በአጭሩ ተቀጭቶበታል።

መሃል አዲስ አበባ በሚገኘው በዚህ የማሰቃያ ቤት ለመስማት የሚከብዱ ግፎች ተፈጽመዋል።

ጥፍር መንቀል፣ የዘር ፍሬ ማኮላሸት፣ ዘቅዝቆ ለቀናት በኤሌክትሪክ ሽቦ ሰውነትን መተልተልና መሰል የስቃይ ተግባራት ዕለታዊ የስራ እንቅስቃሴ ተደርጎ በኢትዮጵያውያን ላይ ግፍ ሲፈጸምበት ለዓመታት የቆየ ቤት ነው ማዕከላዊ።

በኢህ አዴግ ውስጥ የተከሰተውን መሰነጣጠቅ ተከትሎ የለውጥ ሃይሎች በአሸናፊነት ወደ ፊት ሲመጡ ማዕከላዊም ከግፍ ታሪኩ ጋር ሊዘጋ እንደሚችል ተገለጸ።

በስብሰባ የ18 ቀናት ትንቅንቅ ውስጥ የገቡት የኢህአዴግ ማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት ከደረሱባቸው ስምምነቶች አንዱ ማዕከላዊን በመዝጋት ወደ ሙዚየምነት እንዲቀየር ማድረግ ነበር።

በወቅቱ ይህንን ይፋ ያደረጉት አቶ ሃይለማርያም ደሳለኝም ማዕከላዊ ሙዚየም ሆኖ ለታሪክና ለጎብኚዎች ይቀመጣል ማለታቸው ይታወሳል።

 ሆኖም ማዕከላዊ እንደቀድሞም ባይሆን እስረኞችን አላጣም። ማዕከላዊ በይፋ መዘጋቱ ሳይገለጽ ወራት መቆጠሩ ብዙዎች ጥያቄ እንዲያነሱ አድጓል።

ሰሞኑን በመንግስት የመገናኛ ብዙሃን ማዕከላዊን ጨምሮ በተለያዩ ስውር የማሰቃያ እስር ቤቶች የተፈጸሙ ግፎችን የሚተርክ ዘጋቢ ፊልም ለህዝብ ከቀረበ በኋላ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የህግ፣ ፍትህና ዴሞክራሲ ቋሚ ኮሚቴ አባላት ማዕከላዊን ጎብኝተው ነበር።

አባላቱ ከጉብኝታቸው በኋላ በሰጡት መግለጫ ማዕከላዊ በይፋ መዘጋቱን አረጋግጠናል ብለዋል።

 የማሰቃያና የተለያዩ ግፎች የሚፈጽሙባቸውን ክፍሎች ተዘዋውረው የጎበኙት የኮሚቴ አባላት አሁን በማዕከላዊ እሽር ቤቶች የሚገኙት ከቡራዩ የተፈናቀሉ ዜጎች ናቸው፣ በጊዜያዊነት ተጠልለው እየኖሩበት ነው ሲሉ ገልጸዋል።

የኮሚቴው አባላት ማዕከላዊ ከመጋቢት 28 ቀን 2010 ዓ/ም ጀምሮ መዘጋቱንና በአሁኑ ሰአት ምንም እስረኛ እንደሌለ፣ በውስጡ የነበሩ 139 እስረኞችም ወደ አዲስ አበባ ፖሊስ ማረሚያ ቤት በአደራ መልክ መዘዋወራቸውን ተረድተናል ማለታቸውን የመንግስት መገናኛ ብዙሃን ዘገባ ያመለክታል።

የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የህግ፣ ፍትህና ዴሞክራሲ ቋሚ ኮሚቴ አባላት ከማዕከላዊ በተጨማሪ ቃሊቲንና ሌሎች ማረሚያ ቤቶችን ጎብኝተዋል።

በዚህን ወቅት በሙስናና በሰብዓዊ መብት ጥሰት ተጠርጥረው የታሰሩትን ከፍተኛ የሜቴክና የደህንነት ባልስልጣናትን እንዲሁም የቀድሞ የሶማሌ ክልል ፕሬዝዳንትን አነጋግረዋል።

ሰሞኑን ለህዝብ የተላለፈው ዘጋቢ ፊልም ፍርድ ቤት ውሣኔ ባልሰጠበት ክስ ላይ ትኩረት ማድረጉ ያሳደረብን የሞራል ተፅዕኖ ከፍተኛ ነው የሚል ቅሬታ ከሜጀር ጄነራል ክንፈ ዳኘው፣ ከአቶ ያሬድ ዘሪሁንና ከሌሎች ተጠርጣሪዎች መቅረቡንም ለማወቅ ተችሏል።