ሙስሊም ኢትዮጵያውያንን የሚወክል መጅሊስ ለማቋቋም ምርጫ የሚያመቻች ገለልተኛ ኮሚቴ ሊቋቋም ነው

ሙስሊም ኢትዮጵያውያንን የሚወክል መጅሊስ ለማቋቋም ምርጫ የሚያመቻች ገለልተኛ ኮሚቴ ሊቋቋም ነው
(ኢሳት ዜና ሰኔ 27 ቀን 2010 ዓ/ም) ትናንት ማክሰኞ የሙስሊሙ መፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴ አባላት ከጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ጋር በቤተመንግስት ውይይት ካደረጉ በሁዋላ፣ የመጅሊሱ አመራር አባላት በተገኙበት ምርጫውን ለማካሄድ የሚያስችል ገለልተኛ አካል ለማቋቋም ስምምነት ላይ ተድርሷል።
ከሙስሊሙ መፍትሔ አፈላላጊ ኮሚቴ ኡስታዝ አቡበክር አህመድ፣ አሕመዲን ጀበል እና ኡስታዝ ካሚል ሸምሱ፣ ከመጅሊስ ተቀዳሚ ሙፍቲ ሐጂ ዑመር፣ የመጅሊሱ ፕሬዝዳንት ሐጂ ሙሐመድ አሚን እና ሐጂ ከድር፣ ከምሑራን እና ሽማግሌዎች ደግሞ ዶ/ር ኢድሪስ ሙሐመድ፣ ዶ/ር ሙሐመድ ሀቢብ እና ሸኽ ሙሐመድ ጀማል አጎናፍር የኮሚቴው አባላት ሆነው ተመርጠዋል።
ኮሚቴው ምርጫ የሚካሄድበትን መንገድ በዝርዝር አጥንቶ ለመንግስት የሚያቀርብ ሲሆን፣ መንግስትም ለኮሚቴው ሙሉ እውቅና እንደሚሰጥ እና ኮሚቴውን ለማደናቀፍ በሚሞክሩ ግላዊም ሆኑ መንግስታዊ ተቋማት ላይ አስፈላጊውን እርምጃ እንደሚወስድ ታውቋል።