መድረክ በርካታ ህዝብ በተገኘበት የተሳካ ወይይት አደረገ

የካቲት 5 ቀን 2004 ዓ/ም

ኢሳት ዜና:-እሁድ እለት በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ወረዳ 5 ጽ/ ቤት አዳራሽ በአዲሱ የከተማ መሬት አዋጅ ላይ ህዝባዊ ውይይቴ ማካሄዱን በስፍራው የተገኘው  ዘጋቢያችን ገልጧል።

ውይይቱን ዶ/ር መረራ ጉዲና የመሩት ሲሆን የመድረክ የአመራር አባል አቶ ገብሩ አስራት እና በፓርላማ ብቸኛው የተቃዋሚዎች ተወካይ የተከበሩ አቶ ግርማ ሰይፉ በጥናት ላይ የተመሰረተ የውይይት መነበሻ ሃሳቦችን አቅርበዋል፡፡

አቶ ገብሩ አስራት “የከተማን ቦታ በሊዝ ለመያዝ የወጣው አዋጅ ህገ መንግስትን የጣሰና ዜጎችን ለመቆጣጠር ያለመ ነው፣ ኢህአዴግ በኢኮኖሚ ራሱን የቻለን ማህበረሰብ ይፈራል፣ ምክንያቱም ይህ የህብረተሰብ ክፍል ለእርሱ የምርጫ ካርድ እንደማይሆነውና አመለካከቱንም (አብዮታዊ ዴሞክራሲ) እንደማይቀበለው ያውቃልና ፣ ዜጎችን እያደኸየ የመግዛት ስትራቴጂ ይዟል” ብለዋል፡፡

በውይይቱ ላይ ወደ አንድ ሺ የሚጠጉ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ተሳትፈዋል።

አንድ ተሳታፊ ወደ አዳራሹ ሲመጡ የኢህአዴግ ካድሬዎች የማሸማቀቅ፣ የማስፈራራትና የማሳቀቅ ትንኮሳ እንዳደረጉባቸው ገልጸው ፣ “ኢህአዴግ የዓመታት ይዞታችንን፣ መሬታችንን ነጥቆ የእናንተ ንብረት ጣራና ግርግዳ ነው አለን፣ ወደ ፊት ሚስቶቻችንንስ እንደማይነጥቀን ምን ማረጋገጫ አለን?” በማለት አዳራሹን ጠይቀዋል፡፡

በሌላ ዜና ደግሞ አንድነት ፓርቲ ፣ የድርጅቱ ቋሚ ኮሚቴ ባዘጋጀው ከመላ አገሪቱ ለተውጣጡ 55 የፓርቲው አመራሮች ለሁለት ተከታታይ ቀናት ስልጠና መስጠቱን ገልጧል።

ስልጠናው በፓርቲው የፖለቲካ ፣ በህዝብ ግንኙነት ፣ በኢዲቶሪያል ቦርድ ተግባሮች፣ በማህበራዊ ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ፋይናንስ፣ ህግና ሰብአዊ መብት፣ በጽህፈት ቤት አደረጃጀትእና ስለ ድርጅት ጉዳይ ተግባሮች ትኩረት ያደረገ እንደነበር ለማወቅ ተችሎአል።

በፓርቲው የ5 አመት ስትራቴጂ በተጨመሪ በአዲሱ የከተማና ቦታ ሊዝ አዋጅ ዙሪያም ከአመራሮቹ ጋር ውይይት አድርጓል።

ለ20 ሰአታት በተሰጠው ስልጠና ከመላው አገሪቱ የመጡ የአመራር አካላት በፓርቲው እንቅስቃሴ ዙሪያ፣ በሀገሪቱ ወቅታዊ ሁኔታ እና በፓርቲው ስትራቴጂና የአምስት አመት እቅድ ላይ በቂ ግንዛቤ ማግኘታቸው ተመልክቷል።

ፓርቲው ተመሳሳይ ስልጠናዎችን ወደ ተለያዩ ክልሎች በመውረድ ለመስጠት ማቀዱን ለማወቅ ተችሎአል።