መንግስት የብርን ዋጋ በመቀነስ የገጠመውን የውጭ ምንዛሪ እጥረት ለመከላከል የመጨረሻ ጥናት ማዘጋጀቱ ታወቀ

(ኢሳት ዜና–መስከረም 16/2010) በኢትዮጵያ የተደቀነውን ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ እጥረትና አመታዊ የዕዳ ክፍያ በተመለከተ መንግስት የብርን ዋጋ በመቀነስ ለመሻገር የመጨረሻ ጥናት ማዘጋጀቱን የኢሳት ምንጮች ገለጹ።

በዚህ አመት መንግስት ሊከፍለው የሚገባውን ከአንድ ቢሊየን ዶላር በላይ እዳ ለመሸፈን የኢትዮጵያ ሒልተን ሆቴልን ለመሸጥ ሃሳብ መቅረቡም ተመልክቷል።
ኢትዮ-ቴሌኮምን ለኬንያው ሳፋሪ ኮም 50 በመቶ ለመሸጥ አንዳንድ ባለስልጣናት በሚስጥር መነጋገራቸውንም የደረሰን ዜና ያስረዳል።

የብር ዋጋ ቢቀንስ የወጭ ንግድ ይስፋፋል በዚህም ተጨማሪ የውጭ ምንዛሪ ይገኛል በሚል በብሔራዊ ባንክ ገዢ በአቶ ተክለወልድ አጥናፉና በምክትላቸው በአቶ ዮሐንስ አያሌው ተጠንቶ የተዘጋጀው ሰነድ በሕወሃት መሪዎችና በመንግስት ሃላፊዎች ተቀባይነት በማግኘቱ በቅርቡ ከመጨረሻ ማስተካከያ ጋር ተግባራዊ እንደሚሆንም ተመልክቷል።

የቅርብ ምንጮች እንደሚገልጹት የብር የመግዛት ዋጋን ከ10 እስከ 15 በመቶ ለመቀነስ የተሰናዳው ሰነድ የመጨረሻ እልባት በቅርቡ ያገኛል ተብሎ ይጠበቃል።
ተግባራዊ የሚሆነው በመጭው ህዳር ወይንም ታህሳስ ወር ላይ እንደሚሆን ተመልክቷል።

ይህም በሀገሪቱ ምርት የሚሰበሰብበት ወቅት በመሆኑ ተጽእኖው ወዲያው ሊታይ አይችልም በሚል ስልት እንደሆነ ተመልክቷል።

የአንድ የአሜሪካ ዶላርን ህጋዊ ምንዛሪ ከ26 እስከ 30 ብር ያደርሰዋል የተባለው ይህ ለተግባር የደረሰ እቅድ በመስኩ ለተሰማሩ አንዳንድ ባለሙያዎች አሳሳቢነቱ እንደተገለጸላቸው ምንጮች አመልከተዋል።

የብር የመግዛት ዋጋ መቀነስ ወይንም ዲቫልዌሽን በምግብ ሸቀጦች፣በትራንስፖርትና በቤት ኪራይ ላይ እንዲሁም በመድሃኒት ላይ ቀጥተኛ ተጽእኖ ስለሚኖረው ጭማሪ እንደሚከተል ባለሙያዎች አሳስበዋል።
በዚህም በተለይ በቋሚ ገቢ የሚተዳደሩ ደሞዝተኞችና ጡረተኞች ይበልጥ ተጎጂ እንደሚሆኑም ታውቋል።

የሕወሃት ሰዎች ጉዳዩን ለራሳቸው የቅርብ የንግድ ሰዎች አስቀድመው በማሳወቃቸው በጥቁር ገበያ አንድ ዶላርን እስከ 30 ብር እየመነዘሩ የውጭ ምንዛሪ በመሰብሰብ ላይ መሆናቸውንም የኢሳት ምንጮች ገልጸዋል።

በውጭ ምንዛሪ እጥረት፣በወጭ እዳ ክፍያና በበጀት ጉድለት ቀውስ ውስጥ ያለውን ኢኮኖሚ በብር ዋጋ መቀነስ ብቻ መሻገር አይቻልም በሚል የመንግስት ድርጅቶችን የመሸጥ ዕቅድ ወደ መጨረሻው ምዕራፍ እየደረሰ እንደሆነም ተመልክቷል።

በተለይ በግዢና ሽያጭ እንዲሁም መሰል ሂደቶች ከፍተኛ ሀብት በመሰብሰብ የሚጠቀሱትና አሁን የኢንደስትሪውን ዘርፍ የሚመሩት ዶክተር አርከበ እቁባይ ሒልተን ሆቴል እንዲሸጥ ያቀረቡትን ሀሳብ አቶ ሃይለማርያምና ምክትላቸው አቶ ደመቀ መኮንን እንደተቀበሉት ታውቋል።

የብሔራዊ ባንክ ገዢው አቶ ተክለወልድ አጥናፉም ሃሳቡን ደግፈው መቆማቸው ታውቋል።

ለድርጊቱ የመጨረሻ ይሁንታ የሚሰጠው ወይንም የሚያስቆመው የሕወሃት ቡድን በጉዳዩ ላይ የመረጠውን ዝምታ እንደ ይሁንታ በመውሰድ ሒልተን ሆቴል ለሼህ መሀመድ አላሙዲን ይሸጣል ተብሎም በመገለጽ ላይ ይገኛል።

የኢትዮጵያ መርከብ ድርጅትም በዶክተር አርከበ እቁባይ አማካኝነት ለቻይና የሎጅስቲክ ኩባንያ 50 በመቶ ለመሸጥ የቀረበውንና እንደተለመደው አቶ ሃይለማርያም የተስማሙበትን ውሳኔ ያስቆሙት አቶ አርከበን የሚቃወሙትና በስልጣን የበላይ የሆኑት የሕወሃት ሰዎች መሆናቸውንም እነዚሁ ምንጮች ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ መርከብ ድርጅትን ለመሸጥ የቀረበውን ውሳኔ የሕወሃት ቡድን ለምን እንዳስቆመው የታወቀ ነገር ባይኖርም የቀድሞው የኢትዮጵያና የአዲስ አበባ ንግድ ምክር ቤት ፕሬዝዳንት አቶ ክቡር ገና ውሳኔውን በመቃወም ጠንካራ ጽሁፍ መጻፋቸውን ማስታወስ ተችሏል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድና የኢትዮጵያ ቴሌኮሚኒኬሽን ድርጅትስ ምን ዋስትና አላቸው ሲሉም መጠየቃቸው ይታወሳል።

አሁን ባለው መረጃም ኢትዮ-ቴሌኮምን ለኬንያው ሳፋሪ ኮም 50 በመቶ የመሸጥ እቅድ መኖሩንና አንድ የመንግስት ባለስልጣን ከኬንያ ባለስልጣናት ጋር መነጋገራቸውም ታውቋል።

ሆኖም ጉዳዩ በጅምር ላይ ያለና በባለስልጣናትም ሆነ በድርጅት መሪዎች ዘንድ በሚገባ የማይታወቅ እንደሆነም መረዳት ተችሏል።