መንግስት አቡነ መርቆርዮስ ቢመለሱ አልቃወምም ማለቱ ተዘገበ

ታህሳስ ፲፯ (አስራ ሰባት) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም

ኢሳት ዜና:-የፌዴራል ጉዳዮች ሚኒስቴርን ጠቅሶ ሳምንታዊ ሰንደቅ  እንደዘገበው መንግስት በህገ-መንግስቱ መሠረት በሃይማኖቶች የውስጥ ተግባር ጣልቃ መግባት ስለማይችል አቡነ መርቆርዮስ ይመለሱ ወይም አይመለሱ የማለት ህገ-መንግስታዊ መሰረት የለውም።

በመሆኑም በኢትዮጵያ የሚገኘው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ሲኖዶስ፤ <<4ኛው ፓትርያሪክ የነበሩት አቡነ መርቆርዮስ ይመለሱ ብሎ ካመነ  መንግስት ተቃውሞ የለውም>>ብሏል-ሚኒስቴሩ።

የሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ አበበ ወርቁ  መንግስት ለሰላምና ፀጥታ ሲባል የተጀመረውን እርቀ-ሰላምን ሲደግፍ መቆየቱን በመጥቀስ የፓትርያሪክ ምርጫው በሰላምና በመከባበር እንዲሁም በቤተ ክርስቲያኗ ህግ፣ ደንብና መመሪያ እንዲፈፀም ፍላጎት እንዳለው ተናግረዋል።

የፌዴራል ጉዳዮች ሚኒስቴር ‘‘የፓትርያሪክ አሰያየሙ ሰላማዊ ሆኖ እንዲፈፀም፤ ቅሬታ እንዳይፈጥር፣ በሁሉም ምዕመናን ዘንድ ተቀባይነት ያለው የሃይማኖት መሪ እንዲመረጥ ድጋፍ ያደርጋል’’ ያሉት አቶ አበበ ፤ይህንን ድጋፍ በማየት ጥቂት ቀስቃሽ ኃይሎች፦ ‘‘መንግስት በሃይማኖት ጣልቃ ገብቷል’’ እያሉ ቢያራግቡም፤መንግስት  በሂደቱ ግጭት እንዳይፈጥሩ የመከላከል ስራ ከማከናወን ውጪ ያደረገው ነገር የለም ብለዋል።

በሕገ-መንግስቱ ድንጋጌ መሰረት ኃይማኖትና መንግስት የተለያዩ በመሆናቸው ‘‘እገሌ ሹም አገሌን ሻር’’ ብሎ የመወሰን ስልጣኑ ከሃያ አመታት በፊት  አክትሟል ብለዋል- የህዝብ ግንኙነት ሀላፊው።

አቶ አበበ አክለውም፦ ‘‘በዚህች ሀገር ሰላማዊ የአምልኮ ስርዓት እንዳይካሄድ፣ በሃይማኖት መካከል መበጣበጥ ለመፍጠር እና በሃይማኖት ሰበብ አክራሪነትን ለማስፋፋት የሚንቀሳቀሱ ጥቂት ቀስቃሽ  ኃይሎች  ግን የፓትሪያሪኩን ምርጫ ምክንያት በማድረግ ሕዝቡን ውዥንብር ውስጥ በማስገባት በውጪና በውስጥ እንቅስቃሴ እያደረጉ መሆኑን ሚኒስትር መስሪያ ቤቱ ደርሶበታል >>ብለዋል።

‘‘መንግስት ለራሱ የሚጠቅም ፓትርያሪክ ሊሾም ነው፤ በቤተክርስቲያኗ አሰራር ጣልቃ ገብቷል’’ የሚሉ ህገ-ወጥ ቅስቀሳዎች እየተካሄዱ ነው የሚሉት አቶ አበበ፣ ቀስቃሾቹ በሰላማዊ መንገድ ሲወርድ ሲወራረድ የመጣውን ሃይማኖታዊ ስርዓት ለመናድ የሚጥሩ ግለሰቦች መሆናቸውን ተገንዝበናል’’ ብለዋል።

አቶ አበበ  ይህን ቢሉም ፤ለሲኖዶሱ ቅርበት ያላቸው ወገኖች መንግስት “ምርጫውን በሰላማዊ መንገድ ለማስኬድ’’ በሚል ምክንያት የፌዴራል ጉዳዮች ሚኒስቴር ከፍተኛ ባለስልጣን መመደቡን እየገለጹ መሆናቸውን ጋዜጣው  ዘግቧል።

በተለይም በሚኒስትር መስሪያ ቤቱ የሃይማኖትና የእምነት ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት፤ የፓትርያሪኩን ምርጫ በተመለከተ ገደብ ባለፈ ሁኔታ ጣልቃ መግባቱን ለሲኖዶሱ ቅርበት ያላቸው ወገኖች እያወገዙ ነው።

ሲኖዶሱ በስደት ላይ ያሉትን ሊቀ ጳጳስ እንዲመጡ ቢያደርግ የመንግስት አቋም ምን እንደሆነ የተጠየቁት አቶ አበበ፤ <<መንግስት የሚቃወምበት ህገ-መንግስታዊ መሠረት የለውም፤ በጉዳዩም ላይ መንግስት ጣልቃ አይገባም ሲሉ “ምላሽ ሰጥተዋል።

በቅርቡ ፕሬዝዳንት ግርማ ወ/ጊዮርጊስ በአሜሪካ የሚገኙት 4ኛው ፓትርያሪክ ብፁዕ አቡነ መርቆሪዮስ ወደ ሀገር ቤት እንዲመለሱ በደብዳቤ መጠየቃቸውን በተመለከተ የተጠየቁት አቶ አበበ፣ ‘‘ፕሬዝዳንቱ እንደ ግለሰብ ደብዳቤ ፅፈዋል። ምናልባትም ግለሰቦች በሚፈጥሩት ውዥንብር ገብተው፣ ጉዳዩ ወደ ብጥብጥ የሚሄድ መስሏቸው፣ እንዲህ ቢደረግ በሚል ግለሰባዊ እይታቸውን አንፀባርቀው ነበር። ነገር ግን በዚህ ስልጣን ላይ ሆነው ግለሰባዊ ዕይታም ቢሆን መስጠት የማይችሉ መሆኑን ወዲያው ተገንዝበው አርመዋል’’ ሲሉ መልሰዋል።

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ ሰሞኑን ባካሄደው ስብሰባ 6ኛውን ፓትርያሪክ ለመምረጥ አስመራጭ ኮሚቴ አቃቁሟል።

አስመራጭ ኮሚቴውም እስከ ጥር 30 ቀን 2005 ዓ.ም እጩዎችን እንዲያቀርብ በሲኖዶሱ ታዟል። ነገር ግን ከፓትርያሪኩ ምርጫ በፊት ቅዱስ ሲኖዶሱ አስመራጭ ኮሚቴ መሰየሙ በአንዳንድ አባቶች ዘንድ ተቃውሞ ተነስቶበታል።

በአሁኑ ወቅት ከፓትርያሪክ ምርጫው በፊት እርቀ ሰላም ይካሄድ በሚሉና እርቀ ሰላሙ እየተከናወነም ቢሆን የፓትርያሪክ ምርጫው ይከናወን በሚሉ ወገኖች መካከል ልዩነቶች ቢኖሩም፤ በቅርቡ ግን ለስድስት ወራት ክፍት በሆነው ቦታ አዲስ ፓትርያሪክ ይመረጣል ተብሎ ይጠበቃል።

በተመሳሳይ ዜና ደግሞ በአገር ውስጥ ያለው ሲኖዶስ በኢትዮጵያ ያለውን የእስልምና አክራሪነት እንቅስቃሴን የውጩ ሲኖዶስ ሲደግፍ አለማውገዙ እንዳሳዘናቸው የህወሀት አባት የሚባሉት አቶ ስብሀት ነጋ ተናግረዋል። አቶ ስብሀት ከሰንደቅ ጋር ባደረጉት ቃለምልልስ ” የአሜሪካው ሲኖዶስ የእስልምና አክራሪ እንቅስቃሴ በኢትዮጵያ ውስጥ እንደሚደግፍ ይወራል። አገር ውስጥ ያለው ሲኖዶስም የቤተክርስቲያኒቱ ህልውና ቆርቁሮት ተነስቶ ይህን ድርጊት አላወገዘም። የእስልምና አክራሪነት እንቅስቃሴ በኢትዮጵያ ደጋፊ ከሆነም መንግስት እርምጃ መውሰድ ነበረበት።” በማለት ተናግረዋል።

የኦርቶዶክስ እምነት ተከታዮችም ሆኑ ጉዳዩ የሚመለከታቸው አካላት ትኩረት ካልሰጡት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤ/ክ አመራር ለሀይማኖቱም ሆነ ለአጠቃላይ ለስርአቱም አደጋ ወደ መሆን ተቃርቧል በማለት አቶ ስብሀት ገልጸዋል።

አቶ ስብሀት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን የሙስሊሙን የአንድ አመት እንቅስቃሴ አለማውገዟ በቤተከርስቲያኑዋ ህልውና ላይ የተቃጣ አደጋ እንደሆነ አድርገው ማቅረባቸው በግልጽ በሙስሊሙና በክርስቲያኑ መካከል ግጭት ለመፍጠር ማሰባቸውን የሚያሳይ ነው በማለት አንድ ስማቸው እንዳይገለጥ የፈለጉ የሀይማኖት አባት አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።

“የሙስሊሙ እንቅስቃሴ የኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያንን ህልውና የሚነካ ለመሆኑ ማስረጃ የለም” ያሉት እኝሁ አባት፣ በባዶ ሜዳ እንድናወግዝ መጠየቃችን ከበስተጀርባው ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያንን ከሙስሊሙ ጋር ለማጋጨት የታለመ ነገር መኖሩን ያሳያል ሲሉ አክለዋል።

“ለቤተክርስቲያናችን ህልውና አደጋ የሆነው የአቶ ስብሀትና ጓኞቻቸው መንግስት እንጅ ሙስሊሙ ወገናችን አይደለም፣ ሙስሊሙማ  በሀይማኖታችን ጣልቃ አትግቡብን መሪዎቻችንን እኛ እንምረጥ መንግስት አይመረጥብን በማለት እየጮከ ” በማለት አስተያየታቸውን አጠቃለዋል።