መንግስት በአዲስ አበባ የታየውን ከፍተኛ የስንድ እጥረት ለመቅረፍ ከውጭ አገር የገዛውን ስንዴ ለህብረተሰቡ ማከፋፈል ሊጀምር መሆኑ ታወቀ

ኢሳት ዜና:-በቅርቡ በአዲስ አበባ የታየውን ከፍተኛ የስንዴ እጥረት ተከትሎ የዳቦ መጠን መቀነሱን እንዲሁም ህብረተሰቡ ዳቦ ለማግኘት ረጅም ሰአት ተስለፎ መጠበቅ ግድ ብሎት እንደነበር መዘገባችን
ይታወቃል።

ይህን ተከትሎ መንግስት ከዚህ ቀደም ዘይት ለማከፋፈል እንደሞከረው ሁሉ ስንዴም ለነዋሪው በዚህ ሳምንት ውስጥ ማከፋፈል እንደሚጀመር ታውቋል።  አንድ ቤተሰብ በነፍስ ወከፍ የሚገዛው  የስንዴ መጠን ባይታወቅም፣ መረጃዎች እንደሚያመለክቱት ግን ከ25 እስከ 50 ኪሎ ሊደርስ ይችላል።

ግብርናው በከፍተኛ ፍጥነት እንዳደገ በተደጋጋሚ በሚነገርላት ኢትዮጵያ እንድ ዳቦ በቀን በልቶ ለመዋል ጭንቅ እየሆነ መምጣቱን ዘጋቢያችን ገልጧል። ታዋቂው አቤ ቶክቾው በቅርቡ በፍትህ ጋዜጣ ላይ ባሰፈረው ጽሁፍ “ዳቦ አመጹን ተቀላቀለች” በማለት ችግሩን ለመግለጥ ሞክሯል።

የኢትዮጵያ መንግስት ለዳቦ እጥረቱ ዳቦ ጋጋሪዎችን ተጠያቂ በማድረግ ከ60 በላይ ዳቦ ቤቶችን መዝጋቱ ይታወሳል። ዳቦ ጋጋሪዎች በበኩላቸው በአገሪቱ ውስጥ የሚታየው የስንዴ እጥረት ለዳቦ እጥረት መንስኤ ሆኗል ይላሉ። ከወራት በፊት በመላ አገሪቱ ከፍተኛ የሆነ የዘይት እጥረት ተከስቶ እንደነበር ይታወቃል።