መንግስት መምህራን ያቀረቡት የደሞዝ ጥያቄ ለመመለስ ቃል ገባ

የካቲት 15 ቀን 2004 ዓ/ም

ኢሳት ዜና:-የኢትዮጵያ መምህራን ማሕበር ዛሬ በጠራው አስቸኳይ ጠቅላላ ጉባኤ ላይ የተገኙት ትምህርት ሚኒስትሩ አቶ ደመቀ መኮንን በቅርቡም በኢትዮጵያ መምህራን ማህበር በኩል የቀረበው የደሞዝ ማስተካከያ ጥያቄ አግባብነት ያለው በመሆኑ የአገሪቷን የመክፈል አቅም ግምት ውስጥ በማስገባት በጥቂት ጊዜ ውስጥ ምላሽ እንሰጣለን ብለዋል።

የተለጣፊው የኢትዮጵያ መምህራን ማሕበር ፕሬዚዳንት አቶ ዮሐንስ ባንቲ የመምህራን የደረጃ እና የተፈላጊ ችሎታ እድገት ጉዳይ የትምህርቱን ጥራት እየገደለው መሆኑን ተናግረው መንግስት አፋጣኝ መልስ እንዲሰጥ ጠይቀዋል።

መንግስት የመምህራኑን ጥያቄ መቀበሉን ቢያስታውቅም፣ በአጭር ጊዜ ውስጥ የሚለው አነጋገር ለክልል የመምህራን ማህበራት ተወካዮች አልተዋጠላቸውም።

የመምህራኑ ተወካዮች መምህራን የደሞዝ ጭማሪ ሊደረግለቻው ባለመቻሉ ከፍተኛ ችግር ውስጥ መውደቃቸውን በመግለጥ መንግስት ለጥያቄያቸው ቁርጥ ያለ መልስ እንዲሰጥ ሲጠይቁ ቆይተዋል።

የማህበሩ አመራሮች የመንግስትን መልስ ተቀብለው የተባለውን ቀን በትእግስት ይጠብቁ ወይም ጥያቄውን ለመምህራን በማውረድ በአድማ ለማስመለስ ይሞክሩ የተወሰነ ነገር የለም።

በርካታ መምህራን የዛሬውን የመምህራን ጉበኤ ውጤት በጉጉት በመጠባበቅ ላይ ናቸው። በአማራ እና በትግራይ የሚገኙ መምህራን መንግስት ለጥያቄያቸው አፋጣኝ መልስ የማይሰጥ ከሆነ የስራ ማቆም አድማ እንደሚያድረጉ ሲናገሩ መሰንበታቸው ይታወቃል።

መንግስት ለመምህራን ጥያቄ አፋጣኝ መልስ ይሰጣል ተብሎ አይጠበቅም። አሁን በሚታየው የዋጋ ንረት  የደሞዝ ጭማሪ ማድረግ ማለት የዋጋ ንረቱን የባሰ ወደ ሰማይ የሚያጎነው እንደሚሆን ባለሙያዎች ይናገራሉ።

___________________________________________________________________________________________________________________________________________________________________________

ESAT is the first independent Ethiopian satellite service tasked to produce accurate and balanced news and information, as well as other entertainment, sports and cultural programming created for and by Ethiopians.

ESAT is committed to the highest standards of broadcast journalism and programming and will strive to provide an outlet of expression to all segments of the diverse Ethiopian community worldwide