ለደቡብ ሱዳን ተወላጆች ኢትዮጵያዊ ዜግነት ሊሰጥ ነው

(ኢሳት ዲሲ–ግንቦት 9/2010) በመቶ ሺዎች ለሚቆጠሩ የደቡብ ሱዳን ተወላጆች ኢትዮጵያዊ ዜግነት ለመስጠት መወ ሰኑ ተቃውሞ አስነሳ።

የጋምቤላ ክልል ምክር ቤት በፌደራል መንግስቱ የተደረሰውን ስምምነት ለማስፈጸም ውሳኔ ማሳለፉ ታውቋል።

ለደቡብ ሱዳናውያን በጅምላ የኢትዮጵያ ዜግነት እንዲሰጣቸው የተወሰነበት ይፋዊ ምክንያት አልተገለጸም።

የጋምቤላ የመብት ተሟጋቾች ዜግነት የሚሰጣቸው ደቡብ ሱዳናውያን ቁጥራቸው 400ሺህ እንደሚጠጋ ይገልጻሉ።

የኢትዮጵያውያን አኝዋኮችን ህልውና ለማጥፋት የሚደረገውን ሚስጥራዊ እንቅስቃሴ የኢትዮጵያ ህዝብ እንዲያስቆም የመብት ተሟጋቾቹ ጥሪ አቅርበዋል።

ባለፈው ዓመት ነበር በኒውዮርክ የተባበሩት መንግስታት ስብስባ ላይ የተገኙት የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ሃይለማርያም ደሳለኝ የደቡብ ሱዳን ስደተኞችን ችግር ለመፍታት የገንዘብ አቅም ባለመኖሩ በባህሪ፣በቋንቋ ከሚመሳሰሏቸው ጋር መቀላቀል በሚል በስደት ኢትዮጵያ ወስጥ ለሚኖሩ የደቡብ ሱዳን ዜጎች ኢትዮጵያዊ ዜግነት ለመስጠት የተስማሙት።

የአኙዋክ መብት ተከራካሪዎች እንደሚሉት ከሆነ ይህ ጉዳይ ከኢትዮጵያ ህዝብ ተደብቆ ሊፈጸም ዝግጅት እየተደረገ መሆኑ ጠቅሰው የፊዴሬሽን ም ክር ቤት፣በርካታ የጋምቤላ ክልል ምክር ቤት አባላት እንደማያውቁት ይጠቅሳሉ ።

አቶ አዜኑ ጀማል የስደተኞችና ከስደተኛ ተመላሾች ጉዳይ አስተዳደር ዳይሬክተር ከሌሎች ባለስልጣናት ጋር በመሆን ጋምቤላ ተጉዘው መናገራቸው ተጠቅሷል።የጋምቤላ ከልልም ይህንኑ የፌዴራል መንግስተን እቅድ ለማስፈጸም እየተንቀሳቀሰ መሆኑ ተነግሯል።

በአሁኑ ሰዓት በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ የደቡብ ሱዳን ዜጎች በስደተኝነት በኢትዮጵያ የሚኖሩ ሲሆን ለምን ያህሎቹ የኢትዮጵያዊ ዜግነት እንደሚሰጥ በትክክል ባይታወቅም አንዳንድ ወገኖች ቁጥሩን በአስር ሺዎች ሲያደርሱት ሊሎች በመቶ ሺዎች ናቸው በማለት ይናግራሉ።

ለኢሳት ቃለምልልስ የሰጡት የአኙዋክ የልማት ማህበር ጸሀፊ አቶ ኡጁሉ ቻ በርካታ ደቡብ ሱዳናዊያን ከጋምቤላ ክልል መታወቂያ የወሰዱ ሲሆን የኢትዮጵያን ፓስፖርት  የወሰዱም  አንዳሉና በተለያዩ የዓለም ከፍል መኖራቸውን ያነሳሉ። ይህ ሁኔታ በኢትዮጵያ አኙዋኮች ላይ የህልውና አደጋ ደቅኗልም የሚሉት የመብተ ተከራራሪዎቹ ።

ችግሩ የኢትዮጵያ ህዝብ ነው የሚሉት አቶ ኡጁሉ ቻ የኢትዮጵያ ህዝብ ለጉዳዩ ትኩረት በመስጠት ሊጠይቅ ይገባዋል ብለዋል።

ከደቡብ ሱዳን የኢትዮጵያ ድንበር ጥሰው የሚገቡት ደቡብ ሱዳናውያን በተዳጋጋሚ ግዜ የጋምቤላ አኝዋክ ተወላጆችን መግደላቸው፣አፍነው መውሰዳቸው ይታወቃል ።

በተዳጋጋሚ ግዜም በደቡብ ሱዳን ኑዌሮችና በኢትዮጵያ አኙዋኮች መካከል በድንበር አካባቢ በግጦሽ መሬት የተነሳ ከፍተኛ ጸብ መኖሩ ይነሳል ።

ይህ ሁኔታ ባለበት በሺዎች ለሚቆጠሩ ደቡብ ሱዳናውያን ኢትዮጵያዊ ዜግነት መስጠት ችግሩን የከፋ ያደርገዋል የሚሉት አቶ ኡጁሉ ቻ በሂደት የሕገመንግስት ጥያቄ እና የመሬት ባለቤትነት ጉዳይ እንደማይነሳም ማረጋገጫ የለም ሲሉ እሳቸውና የአኝዋክ አክቲቪስቶች ስጋታቸውን ይገልጻሉ።