ለአባይ ግድብ ማሰሪያ ያለፈቃዳቸው ደሞዛቸው የተቆረጠባቸው እና ተቃውሞ ያሰሙ ኢትዮጵያውያን አስፈላጊው የማስተካከያ እርምጃ እንዲወሰድባቸው ተባለ

ሰኔ ፪ (ሁለት) ቀን ፳፻፬ ዓ/ም

ኢሳት ዜና:-ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ የደቡብ ተወላጆች  ለኢሳት እንደገለጡት ያለፈቀዳቸውን ለህዳሴ ግድብ ማሰሪያ  በሚል የተቆረጠው ገንዘብ እንዲመለስላቸው በመጠየቃቸው ነው አስፈላጊው እርምጃ እንዲወሰድባቸው የሚል ደብዳቤ የደረሳቸው።

” የህዳሴን ግድብ ገንዘብ አሰባሰብን ይመለከታል”   በሚል ርእስ በተጻፈው ደብዳቤ ላይ ለግድቡ አናዋጣም ባሉት ላይ አስፈላጊው የማስተካከያ እርምጃ የሚወሰደው ጸረ ልማት ሀይሎች ተብለው በመፈረጃቸው  ነው።

“መንግስት” ይላል የደብዳቤው መግቢያ ” የአባይ ግድብን በመገደብ ሀገራችን የጀመረቸውን የልማት አቅጣጫ ፈጣን እና እውን ለማድረግ በሚያደርገው እንቅስቃሴ የኢትዮጵያ ህዝቦች በውጭም ሀገር በአገር ውስጥ የሚገኙ ቀፏ እንደተመታ ንብ በመንቀሳቀስ የራሳችን አሻራ ያረፈበትን ግድብ መንግስት ካለንበት ድህነት እንላቀቃለን በማለት በየአቅጣጫው ርብርብ እየተደረገ መሆኑ ግልጽ ነው። ስለዚህ ቀና ሀሳብ አይደለም የሰው ልጅና መልአክ፣ ሰይጣንም ግዴታ አለብኝ ብሎ ሳይሳተፍ አይቀርም። በመሆኑም በአገራችን የሚገኙ ብሄር ብሄረሰቦች ተቃዋሚ ፓርቲዎችም ቢሆኑ የልማቱ ጉዳይ የህልውና ጉዳይ መሆኑን ተቀብለው የጋራ አሻራ ለማኖር እየተንቀሳቀሱ ነው።”

ደብዳቤው በማያያዝም ” የመስሪያ ቤታችን ሰራተኞች ቃል ከገቡት የኢትዮጵያ ዜጎች አንዱ ናቸው፣  ከእነዚህ ውስጥ ሁሉም ያለንበትን ሀገራዊ ግዴታ ሊወጣ የእጅ አሻራውን በደሞዙ አማካይነት እያሳረፈ ነው። ነገር ግን የመስሪያ ቤታችን ባልደረባ የሆኑት አቶ …ለአባይ ግድብ የተቆረጠውን ደሞዝ አላግባብ ስለሆነ ፈቃደኛ አይደለሁም እንዲመለስለኝ በማለት የተቀረውን ደሞዝ አልወስድም ብሎአል ሲል ገልጦ ” መንግስት ለሀገር ልማትና እድገት ያስቀመተውን አቅጣጫ ለማፍረስ እንደመንቀሳቀስ ስለሚቆጠር ከጸረ ልማት ሀይሎች ተለይቶ ስለማይታይ በልማት አደናቃፊነት እንደሚፈረጅ ጥርጥር የለንም።” ይላል።

ስለዚህ ይላል ደብዳቤው በመጨረሻም “የመንግስትን የልማት እንቅስቃሴ የህዝቡ የጋራ ተሳትፎ በጸረ ልማት ሀይሎች እንዳይደናቀፍ የአስፈጻሚ አካላት አስፈላጊውን የማስተካከያ እርምጃ እንዲወስድ አሳስባለሁ።”

ይህ ደብዳቤ የደረሳቸው በርካታ ሰራተኞች ከስራ መባረራቸውን፣ አንዳንዶች በእስራት መቀጣታቸውን፣ ሌሎች ደግሞ ደሞዛቸው መቆረጡን ለኢሳት ገልጠዋል። አሁንም ድረስ እየተዋከቡ እንደሚገኙ የገለጡት ሰራተኞች በዚህ አቋማችን ብቻ ከስራችን ተባረን ቤተሰቦቻችንን ለአደጋ አጋልጠን እንገኛለን ሲሉ ተናግረዋል።

መንግስት የኢትዮጵያ ህዝብ በፈቃደኝነት ለአባይ ግድብ መዋጮ እየከፈለ መሆኑን በተደጋጋሚ ቢገልጥም፣ በመሬት ላይ ያለው እውነታ ግን ከዚህ ይለያል። ቦንድ ለመግዛት አቅም የለንም ያሉ አርሶአደሮችም በልማት አደናቃፊነት ለእስር እየተዳረጉ ነው። በአማራ ክልል አዲስ የተጣለውን 500 ብር ቦንድ ለመግዛት የተሳናቸው አርሶአደሮች፣ ከብቶቻቸው ሳይቀር እየተነዳ ለእስር እየተዳረጉ ነው።

በቅርቡ በሀብት ደረጃው የተሻሉ የሚባሉት የግንባታ ተቋራጮች ለቦንድ ግዢ ቃል የገቡትን አንድ አስረኛውን ያክል እንኳ አለመክፈላቸው መዘገቡ ይታወሳል። ትለቅ ተስፋ የተጣለባቸው ሼክ ሙሀመድ ሁሴን አላሙዲንም ተጭበርብሬአለሁ በሚል ለቦንድ ግዢ ቃል የገቡትን ክፍያ አብዛኛውን ገንዘብ አላስገቡም።

___________________________________________________________________________________________________________________________________________________

ESAT is the first independent Ethiopian satellite service tasked to produce accurate and balanced news and information, as well as other entertainment, sports and cultural programming created for and by Ethiopians.

ESAT is committed to the highest standards of broadcast journalism and programming and will strive to provide an outlet of expression to all segments of the diverse Ethiopian community worldwide