ለሞባይል ስርጭት ጥራት መጋደል የአዲስ አበባ ህንጻዎች ምክንያት ናቸው ተባለ

ታህሳስ  ፳፮(ሃያ ስድስት) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም

ኢሳት ዜና:-ላለፉት ሁለት ዓመታት በፍራንስ ቴሌኮም ኩባንያ የማኔጅመንት አባላት ሲተዳደር የቆየው ኢትዮ-ቴሌኮም በአዲስአበባ
የሕንጻዎች ግንባታ መበራከት ጋር ተያይዞ የሞባይል አገልግሎት ጥራት ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ ማሳደሩን በይፋ
ገለጸ፡፡

የፍራንስ ቴሌኮም የማኔጅመንት አባላት ኮንትራት መጠናቀቅን አስመልክቶ ከሁለት ቀናት በፊት  በሸራተን ሆቴል
በተሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ የተገኙት ምክትል ጠ/ሚኒስትርና የመገኛና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዶ/ር
ደብረጽዮን ገ/ሚካኤል እንደተናገሩት የሞባይል ማሰራጫ ታወሮች ለመትከል ጥናት ሲደረግና ሲተከል ያልነበሩ
ሕንጻዎች በድንገት ተገንብተው ታወሩን ስለሚጋርዱ በከተማው የሞባይል ስርጭት ላይ መስተጓጎል እየፈጠረ ነው። ዶ/ር ደብረጽዮን የአዲስአበባ ሞባይል ጥራት መጓደል ትልቁ ምክንያት ይህው ነው ብለዋል፡፡
ችግሩን ለመቅረፍ በሕንጻዎቹ ላይ ማሰራጫዎቹን መትከል እንደሚያስፈልግ፣ይህን ለመፈጸምም የሕንጻዎቹ ባለንብረቶች
ፍቃድ አስፈላጊ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡ይህም ሆኖ ጥቂት የማይባሉ ባለንብረቶች ከግንዛቤ ጉድለት የተነሳ ለመተባበር
ፈቃደኛ አልሆኑም፡፡ ባለንብረቶቹ የሞባይል ማሰራጫ አንቴናው በሕንጻው ላይ ቢተከል ፎቁ የሚፈርስ ወይም አደጋ
የሚደርስበት አድርገው ማሰባቸው ትልቁ ምክንያት መሆኑን ገልጸዋል፡፡
አቶ አብዱራሂም አህመድ የኢትዮ ቴሌኮም የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ በበኩላቸው በአዲስአበባ ብቻ ወደ 35 የሚጠጉ
ሕንጻዎች ላይ ኩባንያው ችግር እንዳጋጠመው አምነዋል፡፡ በሕንጻው ላይ አንቴና ቢተከል በቅድሚያ የሚጠቀመው
የሕንጻው ባለቤትን ጨምሮ በሕንጻው የሚገለገሉትና የአካባቢው ሰዎች ናቸው ያሉት ኃላፊው ባለቤቶቹ አንቴና
ለመትከል ሲጠየቁ የተጋነነ ክፍያ በመጠየቅና የተለያዩ ሰበቦችን በመፍጠር እንዳይተከል የማድረግ አማራጭን
ይከተላሉ በማለት አስረድተዋል፡፡
ኢትዮ ቴሌኮም ላለፉት ሁለት ዓመት ተኩል ጊዜያት ማኔጅመንቱን ለፍራንስ ቴሌኮም ኩባንያ ሰጥቶ ከቆየ በኋላ
በአሁኑ ወቅት ማኔጅመንቱ ሙሉ በሙሉ በኢትዮጵያዊያን እንዲያዝ ማድረጉን ገልጾአል፡፡ በአሁኑ ወቅት ዋና ስራ
አስፈጻሚ በመሆን ሲያገለግሉ የቆዩት ፈረንሳዊ ለመጪዎቹ ስድስት ወራት ብቻ በአማካሪነት ለመቆየት መቀጠራቸውን
ተገልጾአል፡፡
የፈንሳዩ ኩባንያ የኢትዮ ቴሌኮምን ማኔጅመንት ከመረከቡ በፊት በዓመት ሰባት ቢሊየን ብር ይሰበሰብ የነበረው ገቢ
አምና ወደ 12 ቢሊየን ብር ማደጉን፤ በ2005 በጀት ዓመት የመጀመሪያዎቹ አምስት ወራት ብቻ ሰባት ቢሊየን ብር
ገቢ መሰብሰቡን እንደስኬት ዶ/ር ደብረጽዮን ቢናገሩትም የቴሌኮም አገልግሎት ጥራት ማሽቆልቆል ጉዳይ ከጋዜጠኞች
በከፍተኛ ደረጃ በምሬት ጭምር የቀረበ ጥያቄ ሆኗል፡፡ ዶ/ሩ የአገልግሎት ጥራት መጓደል መኖሩን በማመን ጥራትን
ለማሻሻል ሌት ተቀን እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

አዲሱን የቴሌ ማኔጅመንት የተረከቡት አብዛኞቹ በልዩ ሁኔታ የሰለጠኑ የህወሀት ታጋዮች መሆናቸውን መዘገባችን ይታወሳል።