ፕሮፌሰር ሪቻርድ ፓንክረስት በ90 አመታቸው አረፉ

ኢሳት (የካቲት 9: 2009)

በኢትዮጵያ ታሪክ ለረጅም አመታት ጥናትና ምርምር በማካሄድ የሚታወቁት ታዋቂው የኢትዮጵያ ወዳጅ ፕሮፌሰር ሪቻርድ ፓንክረስት በ90 አመታቸው አረፉ።

የኢትዮጵያ ጥናትና ምርምር ኢንስትቲዩት በመመስረት የሚታወቁት የብሪታኒያ ዜግነት ያላቸው ፕሮፌሰር ፓንክረስት እንደፈረንጆቹ አቆጣጠር ከ1950ዎቹ መጨረሻ ጀምሮ ከቤተሰቦቻቸው ጋር በኢትዮጵያ መኖር እንዲጀምሩ ስለህይወታቸው ከተጻፉ ታሪኮች ለመረዳት ተችሏል።

በኢትዮጵያ ታሪክ ዙሪያ ከ20 በላይ መጽሃፎችን በማሳተም ለአለም ለንባብ ያበቁት የታሪክ ምሁሩ ለበርካታ አመታት ላደረጉት የታሪክ አስተዋጽዖ ከአጼ ሃይለስላሴ ሽልማት ድርጅቶችና ከእንግሊዝ መንግስት የወርቅ ሜዳሊያና ኒሻን ለመሸለም እንደበቁም ታውቋል።

ፕሮፌሰር ሪቻርድ ፓንክረስት ለአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ከ50 አመት በላይ የሰጡት ምሁራዊ አስተዋጽዖ ዩኒቨርስቲው ዛሬ ለደረሰበት የእድገት ምዕራፍ ትልቅ ሚና መጫወቱም ይነገራል።

ከጥቂት አመታት በፊት የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የተመራማሪነት ብቃታቸውን በማረጋገጥ የፕሮፌሰርነትና የክብር ዶክትሬት ዲግሪ ማዕረግ የሰጣቸው ሲሆን፣ የታሪክ ምሁሩ በአለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃን በኩል የኢትዮጵያ ታሪክን አስመልክቶ በርካታ ጽሁፎችን ሲጽፉ እንደነበር ታውቋል።

እንደፈረጆቹ አቆጣጠር በወርሃ ዴሴምበር 3 ፥ 1927 የተወለዱት ፕሮፌሰር ሪቻርድ ፓንክረስት፣ እናታቸው ሲልቪያ ፓንክረስት ለኢትዮጵያ የነበራቸው ፍቅር ለፕሮፌሰሩ ከፍተኛ አስተዋጽዖ እንዳደረገ ይነገራል።

በ90 አመታቸው ሃሙስ ከዚህ አለም የተለዩት ፕሮፌሰር ሪቻርድ ፓንክረስት በአጠቃላይ በኢትዮጵያ ታሪክ ወደ 400 አካባቢ ጽሁፎችን ለአለም አቀፍ መጽሄት ሲያቀርቡ 22 መጽሃፍቶችን በትብብር እንዲሁም 17 መጽሃፍቶችን በራሳቸው እንደጻፉ ከታሪካቸው ለመረዳት ተችሏል።

የአክሱም ሃውልት ከጣሊያን ወደ ኢትዮጵያ እንዲመለስ በተደረገው ጥረትም፣ ፕሮፌሰር ሪቻርድ ከፍተኛ አስተዋጽዖ የነብራቸው ሲሆን፣ በኢትዮጵያ ቆይታቸው ከባለቤታቸው ሪታ ፓንክረስት ሁለት ልጆች እንዳሏቸው ታውቋል።