የኢቢሲ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ስራ ለቀቁ

(ኢሳት ዲሲ–ግንቦት 14/2011)የኢትዮጵያ ብሮድካስት ኮርፖሬሽን /ኢቢሲ / ዋና ሥራ አስፈጻሚ  አቶ ስዩም መኮንን ከኃላፊነታቸው መልቀቃቸውን ለድርጅቱ ሰራተኞች አሳወቁ ። ዶክተር ንጉሴ ምትኩ ሊተኳዋቸው እንደሚችሉ የኢሳት ምንጮች ተናገሩ   ።

ከ2008 ዓም ጀምሮ የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሸን (ኢቢሲ) ዋና ሥራ አስፈጻሚ በመሆን ሲያገለግሉ የቆዩት አቶ ሥዩም መኮንን በትላንትናው እለት  ግንቦት 13 ቀን 2011 ዓ.ም. ከኃላፊነታቸው መልቀቃቸውን ለድርጀቱ ሠራተኞች አስታወቁ፡፡

አቶ ሥዩም የኮርፖሬሸኑን የዘጠኝ ወራት የሥራ አፈጻጸም አስመልክቶ፣ በኢትዮጵያ ሆቴል ከሠራተኞች ጋር ውይይት ማድረጋቸውና በዚሁ የውይይት መድረክ ላይ ድርጅቱን መልቀቃቸውን አሳውቀዋል።

አቶ ስዩም ድርጅቱን ስለመልቀቃቸው ቢናገሩም ለመልቀቃቸው የሰጡት ምክንያትና ዝርዝር ነገር እንደሌለ ለማወቅ ተችሏል ።

መልቀቃቸውን ለሰራተኛው ባሳወቁበት ሰዓት  የድርጀቱ ሰራተኞች በከፍተኛ ጭብጨባ ስሜታቸውን መግለጻቸውን የተገኘው መረጃ ያመለክታል። ለድጋፍ ይሁን ለተቃውሞ እንደሆነ ባይታወቅም።

አቶ ሥዩም መኮንን ከ2008 ዓ.ም. ጀምሮ ኮርፖሬሽኑን በዋና ሥራ አስፈጻሚነት ሲመሩ መቆየታቸውና በድርጅቱ ውስጥ ለውጦችን ማምጣታቸው ይነገርላቸዋል። በሌላ በኩልም ተቃውሞዎች እንደነበሩባቸው ይነገራል፡፡

አቶ ስዩም መኮንን  የአማራ መገናኛ ብዙኃን ቢሮ ኃላፊ፣ እንዲሁም በአማራ ክልል የደቡብ ወሎ ዞን አስተዳዳሪ ሆነው መስራታቸው ይታወቃል።

አቶ ስዩም ከሀላፊነታቸው መለቀቃቸውን ተከትሎ  የደብረ ማርቆስ ዩንቨርስቲ  ፕሬዝዳንት የነበሩት ዶክተር ንጉሴ ምትኩ ሊተኳቸው እንደሚችሉ የኢሳት ምንጮች ተናግረዋል።