ግሎባል አሊያንስ ለሀገር ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያደረገ መሆኑ ተገለጸ

(ኢሳት ዲሲ–ግንቦት 9/2011)የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ግሎባል አሊያንስ እያደረገ ያለውን ሀገራዊ አስተዋጽኦ ታላቅ ተግባር ነው ሲሉ አወደሱት።

ዓለም ዓቀፍ ትብብር ለኢትዮጵያውያን መብት ግሎባል አሊያንስ ከተባበሩት መንግስታት ድርጅትና ከወርልድ ቪዥን ኢትዮጵያ ጋር ውይይት አደረገ።

ባለፈው ረቡዕ ለጌዲዮ ተፈናቃዮች የ31 ሚሊዮን ብር ድጋፍ ያደረገው ግሎባል አሊያንስ በውጭ በሚገኙ ኢትዮጵያውያንና በመንግስት መካከል መልካም ግንኙነት እንዲኖር የሚያስችል እንቅስቃሴ በማድረግ ላይ መሆኑን ገልጿል።

የግሎባል አሊያንስ የኢትዮጵያ ተወካይ ወይዘሮ ትዕግስት ካሳ ለኢሳት እንደገለጹት ከመንግስትና ከዓለም ዓቀፍ ተቋማት ጋር የተደረጉት ውይይቶች ለግሎባል አሊያንስ ቀጣይ ሀገራዊ ተግባር ከፍተኛ አቅም የሚፈጡ ናቸው።

ዓለም ዓቀፍ ትብብር ለኢትዮጵያውያን መብት ግሎባል አሊያንስ ዛሬ ከመንግስትና ከዓለም ዓቀፍ ተቋማት ጋር በመገናኘት በኢትዮጵያ ተፈናቃዮችን መልሶ በማቋቋም አንጻር ውይይት አድርጓል።

በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መስሪያ ቤት የተገኙት የግሎባል አሊያንስ ተወካዮች ከሚኒስትሩ አቶ ገዱ አንዳርጋቸው ጋር ተገናኝተዋል።

በውይይቱ ሚኒስትሩ የግሎባል አሊያንስን ጥረት አድንቀው ምስጋና አቅርበዋል።

ከውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ገዱ አንዳርጋቸው ጋር የተገናኙት የግሎባል አሊያንስ አመራር አባል አቶ በትሩ ገብረ እግዚአብሔር ለወገን ደራሽ ወገን ነው የሚለውን አስመስክራችኋል የሚል አድናቆት እንዳገኙ ለኢሳት ገልጸዋል።

ዓለም ዓቀፍ ትብብር ለኢትዮጵያውያን መብት በሀገር ቤት መዋቅር ከፍቶ ህጋዊ ሰውነት ለማግኘት እየሰራ መሆኑን ገልጿል።

በኢትዮጵያ የግሎባል አሊያንስ ተወካይ ወይዘሮ ትዕግስት ካሳ በዛሬው ዕለት ከሶስት አካላት ጋር የተደረገውን ውይይት ውጤታማ ሲሉ ገልጸውታል።

ከወርልድ ቪዥን ኢትዮጵያና ከመንግስታቱ ድርጅት የሰብዓዊ እርዳታ መስሪያ ቤት ኦቻ ጋር የተደረጉት ውይይቶች ለግሎባል አሊያንስ ቀጣይ ስራ ግብዓት ይሆናል ነው ያሉት ወይዘሮ ትዕግስት።

ዓለም ዓቀፍ ትብብር ለኢትዮጵያውያን መብት ግሎባል አሊያንስ በውጭ የሚገኙ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ከአገራቸው ጋር ያላቸው ቁርኝት እንዲቀጥል እየሰራ እንደሚገኝ አርቲስትና አክቲቪስት ታማኝ በየነ ለውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ገዱ አንዳርጋቸው ገልጿል።

በጎ ፈቃደኛ የዲያስፖራ አባላትን በማሰባሰብ ወደ ኢትዮጵያ መጥተው በሙያቸው የድጋፍና የስልጠና እገዛ እንዲሰጡ እያደረገ መሆኑንም ተናግሯል።

ግሎባል አሊያን ባለፈው ረቡዕ በአዲስ አበባ በተከናወነ ስነስርዓት በጊዲዮ ለተፈናቀሉ ወገኖች መልሶ ማቋቋሚያ የሚሆን የ31 ሚሊየን ብር ድጋፍ ማድረጉ የሚታወስ ነው።