ዶ/ር ቴዎድሮስ የኮሌራ በሽታ እንዳይታወቅ ደብቀዋል ተብለው በአለም አቀፍ የጤና ባለሙያዎች ክስ ቀረበባቸው

ኢሳት (ግንቦት 7 ፥ 2009)

ኢትዮጵያን በመወከል ለአለም ጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተርነት ተፎካካሪ ሆነው የቀረቡት ዶ/ር ቴዎድሮስ አድሃኖም የጤና ጥበቃ ሚኒስትር በነበሩ ጊዜ በሃገራቸው የተከሰቱ ሶስት የኮሌራ ወረርሽኝ በሽታዎች ለህዝብ እንዳይታወቅ አድርገዋል የሚል ቅሬታ በአለም አቀፍ የጤና ባለሙያዎች ቀረበባቸው። 

የጤና ድርጅቱ አባል ሃገራት የመጨረሻ እጩ ሆነው ከቀረቡ ሶስት ተፎካካሪዎች መካከል አንዱን ለመምረጥ የሳምንት ዕድሜ በቀራቸው ጊዜ ዶ/ር ቴዎድሮስ ላይ የቀረበው ቅሬታ በምርጫው ሂደት ላይ ከፍተኛ ተፅዕኖን ሊያሳድርባቸው ይችላል ሲል ኒውዮርክ ታይምስ ጋዜጣ ዘግቧል።

በአሜሪካ በሚገኘው የጆርጅታውን ዩኒቨርስቲ የኦ ኔል ኢንስቲትዩት ፎር ናሽናል ኤንድ ግሎባል ኸልዝ ሎው ዳይሬተር እና የብሪታኒያው ተፎካካሪ የሆኑት ሎረንስ ጎስተን የአለም ጤና ድርጅት በሃገሩ የበሽታ መከሰትን በደበቀ ተፎካካሪ የሚመራ ከሆነ ተቋሙ ተአማኒነቱን ያጣል የሚል ስጋት ስላደረባቸው ሁኔታውን ይፋ ማድረግ እንደተገደዱ ገልጸዋል።

መረጃውን ይፋ ባደረጉ ጊዜ አማካሪ የሆኗቸውን የብሪታኒያውን ተፎካካሪ ዶ/ር ዴቪድ ናባሮው በጉዳዩ እንዳላማከሯቸው እና ድርጊቱን በሃላፊነት ስሜት እንዲታወቅ ማድረጋቸውን እንደተናገሩ ኒውዮርክ ታይምስ ጋዜጣ አስነብቧል።

ዶ/ር ቴዎድሮስ አድሃኖም በበኩላቸው የቀረበባቸውን ቅሬታ በማስተባበል በመጨረሻ ሰዓት የብሪታኒያ የጤና ሃላፊዎች ከፍተውታል ያሉትን የስም ማጥፋት ዘመቻ እንዳሳሰባቸው ምላሾን ሰጥተዋል።

የብሪታኒያው ተፎካካሪ ዶ/ር ናባሮው  ቅሬታው በዶ/ር ቴዎድሮስ ላይ እንዲቀርብ የሰጡት ትዕዛዝ አለመኖሩን ለጋዜጣው አስረድተዋል።

የአለም ጤና ባለስልጣናት አሁንም ድረስ በኢትዮጵያ ተከስቶ ያለው የኮሌራ በሽታ እንዳይታወቅ መደረጉን በአግባቡ የሚያውቁት ጉዳይ ነው ሲሉ ተፎካካሪው አክለው ገልጸዋል።

በኢትዮጵያ የሶማሌ ክልል ቁጥራቸው ያልተገለጸ ሰዎች በመሞት ላይ መሆናቸውን የተባባሩት መንግስታት ድርጅት የእርዳታ ማስተባበሪያ ቢሮ ሲገልፅ ቆይቷል።

የፌዴራል እና የሶማሌ ክልል ባለስልጣናት ወረርሽኙ በሰው ላይ ጉዳት እያደረሰ መሆኑን ቢያረጋግጡም ምን ያህል ሰው በበሽታው እንደሞተ የሰጡት ዝርዝር መረጃ የለም። ባለፈው አመት ክረምት ወቅት በአዲስ አበባ ተመሳሳይ መልክ ተከስቶ የነበረው የኮሌራ በሽታ ወረርሽኝ በሰው ዘንድ የሞት ጉዳትን ቢያስከትልም የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ጉዳቱ ለህዝብ መግለፅ ድንጋጤን ይፈጥራል በማለት መረጃው እንዳይሰራጭ አድርጎ እንደነበር የሚታወስ ነው።

ቅሬታን ያቀረቡት የጤና ባለሙያው ሎረንስ ጎስቲን ኢትዮጵያ የበሽታ ወረርሽኝን በመደበቅ ያላት የቆየ ታሪክ ትኩረት ሊሰጠው የሚገባው ጉዳይ ነው ሲሉ አክለው አስረድተዋል።

እነዚሁ የበሽታ ስርጭቶች በዶ/ር ቴዎድሮስ የጤና ጥበቃ ሚኒስትር በነበሩ ጊዜ ሁሉ የተከሰቱና የተሸሸጉ ናቸው በማለት የጤና ባለሙያው ለኒውዮርክ ታይምስ ጋዜጣ አስታውቀዋል።

ለሰባት አመታት ያህል የጤና ጥበቃ ሚኒስትር ሆነው ያገለገሉት ዶ/ር ቴዎድሮስ አድሃኖም በተለያዩ አመታት ሶስት ጊዜ ተከስተው የነበሩ የአጣዳፊና ተቅማት በሽታዎች ኮሌራ ሊባሉ የማይችሉ እንደነበሩ ለጋዜጣው በሰጡት ምላሽ ተናግረዋል።

ይሁንና የአለም ጤና ድርጅት ባለስልጣናት የኢትዮጵያ ባለስልጣናት የተከሰቱ በሽታዎችን ሁኔታ በአግባቡ እንደማይገልፁ በግል ቅሬታን እንዳቀረቡም ኒውዮርክ ታይምስ ጋዜጣ በዘገባው አስፍሯል።

የአጣዳፊ ተቅማጥ እና ትውከት በሽታ ከሁለት ሳምንት በላይ መሻሻልን ካላሳየ በሽታው ወደ ኮሌራ የመለወጥ ሂደት እንዳለው የጤና ባለሙያዎች ይገልጻሉ።

ዘጋርዲያን እና ዋሽንግተን ፖስት ጋዜጣዎች ስማቸው ያልተገለፀ ባለስልጣናት የእርዳታ ድርጅቶች ኮሌራ የሚለውን ቃል እና የታማሚዎችን ቁጥር ከመግለፅ እንዲቆጠቡ ግፊት ያደርጉ እንደነበር መዘገባቸውንም ኒውዮርክ ታይምስ ጋዜጣ አውስቷል።

ይሁንና ከኢትዮጵያ ውጭ በተካሄደ የላብራቶሪ ምርመራ በሽታው የኮሌራ ባክቴሪያ ተገኝቶበት እንደነበር ጋዜጣው ዘግቧል። የአለም ጤና ድርጅት አባል ሃገራቱ በሽታዎች ሲከሰቱ ሁኔታዎችን በግልፅ ይፋ እንዲያደርጉ የሚጠይቅ መመሪያና ደንብ ያለው ሲሆን፣ አባል ሃገራት የበሽታ ስርጭትን በአግባቡ ሳያውቁ ሲቀር በድርጅቱ ተአማኒነት እንደማያገኙ ይነገራል።

ዶ/ር ቴዎድሮስ አድሃኖም የተፎካካሪያቸው የዶ/ር ናባሮው ደጋፊዎች የቅኝ ገዢነት አስተሳሰብ ያላቸውና የታዳጊ ሃገራት ተወካይን ዋጋ የማሳጣት አላማ ያላቸው ናቸው ሲሉ አክለው ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ፣ የብሪታኒያና፣ የፓኪስታን ተፎካካሪዎች የመጨረሻ ዕጩ ሆነው የቀረቡ ሲሆን፣ የጤና ድርጅቱ አባል ሃገራት በቀጣዩ ሳምንት ምርጫን ያካሄዳሉ ተብሎ ይጠበቃል።