ዲቪ ሎተሪ ተጀመረ

(ኢሳት ዲሲ–መስከረም 23/2011) የ2020 የዲቪ ሎተሪ ዛሬ ተጀመረ።
ከአፍሪካ ሃገራት ለናይጄሪያ እንዲሁም ከሩቅ ምስራቅ ለቻይናውያን እድል የነፈገው የዚህ አመት ዲቪ ሎተሪ ለአንድ ወር ያህል የሚቀጥል መሆኑም ታውቋል።


ባለፉት 20 ያህል አመታት ከ1 ሚሊየን በላይ የውጭ ሃገራት ዜጎች በዲቪ ሎተሪ አሜሪካ መግባታቸውም ታውቋል።
በአመት እስከ 55ሺ ለሚሆኑ ሰዎች በሚሰጠው እድል እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር ከ1995 ጀምሮ በዲቪ ሎተሪ አሜሪካ በመግባት ከአለም ሃገራት ግንባር ቀደም ሆነው የተገኙት ኢትዮጵያውያን መሆናቸውንም የአሜሪካ ኮንግረስ ሪፖርቶች አመልክተዋል።
ከዛሬ ረቡዕ መስከረም 23/2011 እስከ ጥቅምት 27/2011 በሚቆየው ዲቪ ሎተሪ ከተወሰኑ ሃገራት ዜጎች በቀር በመላው አለም የሚገኙ ሁሉ የእድሉ ተጠቃሚ ይሆናሉ።
ናይጄሪያ፣ቻይና፣ካናዳ፣ሕንድ፣ብሪታኒያና ደቡብ ኮሪያን ጨምሮ የ18 ሃገራት ዜጎች ብቻ በእድሉ እንደማይጠቀሙ በይፋ ተገልጿል።
የእነዚህ ሃገራት ዜጎች የእድሉ ተጠቃሚ የማይሆኑት ምክንያትም በቀደሙት 5 አመታት ብቻ ከነዚህ ሃገራት ከ50ሺ በላይ ስደተኞች ወደ አሜሪካ በመግባታቸው እንደሆነም መረዳት ተችሏል።
በየአመቱ ለ50ሺ ያህል እድለኞች በሚሰጠው የዲቪ ሎተሪ ኢትዮጵያውያን በተጠቃሚነት ግንባር ቀደም ሆነው ተገኝተዋል።
ከአሜሪካ ኮንግረስ ሪፖርት መረዳት እንደተቻለው ፕሮግራሙ ከተጀመረበት እንደ አውሮፓውያኑ ከ1995 እስከ 2016 በአጠቃላይ 1 ሚሊየን 40ሺ 264 ሰዎች ከመላው አለም እጣው ደርሷቸው አሜሪካ ገብተዋል።
ባለፈው የካቲት ወር ይፋ የሆነው የኮንግረሱ ሪፖርት እንደተመለከተው ከነዚህ ውስጥ 65ሺ 224ቱ ኢትዮጵያውያን ናቸው።
በዲቪ ሎተሪ በዚህ ቁጥር አሜሪካ የገባ የሌላ ሃገር ዜጋ ባለመኖሩ ኢትዮጵያውያን ቀዳሚ ሆነው ተገኝተዋል።
ከኢትዮጵያ ቀጥሎ 58ሺ 548 በማስገባት ናይጄሪያ ስትከተል ግብጽና ዩክሬን 53ሺና 50ሺ ያህል በማስመዝገብ ተከታይ ሆነዋል።
ጋና፣ሩሲያ፣ ኬንያ፣ኢራን፣ፖላንድ፣ቱርክ ከ20ሺ በላይ በማስመዝገብ ከቀዳሚዎቹ 20 ሃገራት ውስጥ ተቀምጠዋል።
እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር ከ1995 ጀምሮ በቀጠለው እጣ ኢትዮጵያውያን ያለማቋረጥ ከ2ሺ እስከ 3ሺ 548 በአመት እድሉ ሲደርሳቸው ቆይቷል።
ከኮንግረሱ ሪፖርት መረዳት እንደተቻለው ኢትዮጵያውያን ከ2ሺ ያነሰ ቁጥር የደረሳቸው እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ2012 ሲሆን በዚህ አመት ኢትዮጵያውያን የእድሉ አሸናፊዎች ቁጥር 1 ሺ 718 ነበር።
ከፍተኛው ቁጥር ደግም እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ1996 ሲሆን ቁጥሩም 3ሺ 548 እንደሆነም መረጃው አመልክቷል።